የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎች የሀገርን እድገት በማነጽ ረገድ መሰረታዊ ስኬቶችን እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎች የሀገርን እድገት በማነጽ ረገድ መሰረታዊ ስኬቶችን እያስመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎች የሀገርን እድገት በማነጽ ረገድ መሰረታዊ ስኬቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም 2026 በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁልጊዜም ችግሮችን በጽናት እና በድል በማለፍ የመገንባት ታሪክ መሆኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ትልቅ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የተደረጉ ጠንካራ ሪፎርሞች የውጭ ምንዛሬ ገበያ አሠራር መሻሻልና አቅርቦት ማደግ፣ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣት፣ የወጪ ንግድ እና የመንግሥት ገቢ ማደግ፣ የግል ኢንቨስትመንት እንቅፋቶች መፈታት፣ የገንዘብ ፖሊሲ ዘመናዊነትና የፋይናንስ ዘርፍ ደንብን በማጠናከር ተጨባጭ ወጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
እነዚህ ስኬታማ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሀገሪቱን ወደ ትልቅ የኢኮኖሚ ሽግግር እየመራት እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ለውጥ ትክክለኛ መለኪያው በወረቀት ላይ በሚሰፍሩ ሪፖርቶች ብቻ ሳይሆን፣ መሬት ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ፋይናንስ ማግኘት የሚችሉ አርሶ አደሮች፣ ኩባንያ መመስረት የሚጥሩ ወጣቶች፣ ብድር አግኝተው ንግድን ማስፋት የሚችሉ ሴት ኢንተርፕሩነር እንዲሁም የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉ ባለሀብቶች መኖራቸው የለውጡ እውነተኛ መለኪያዎች ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በአንድ ክስተት ወይም ቅጽበት ላይ ብቻ የተገነባ ሳይሆን፤ በተቋማት፣ በህጎች፣ በገበያዎች፣ በመሠረተ ልማት፣ በሰዎች አቅምና ከዕለታዊ ፖለቲካ በላቀ መልኩ በጠንካራ የለውጥ ሂደት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አብራርተዋል።
ለዚህም መንግስት ዕድገትን፣ የለውጥ ፍጥነት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ዲሲፕሊንን ማስጠበቅ፣ አደጋዎችን ቀድሞ በመገመት በአግባቡ ማስተዳደር ላይ ቁርጠኝነት እንዳለው አረጋግጠዋል።
በመሆኑም አካታችነት ዋናው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሆኖ፤ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች እና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች የዚህ ዕድገት ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ይህም መንግሥት ሕጎችን ሲያዘጋጅ፣ ተቆጣጣሪዎች ፈጠራን ሳይገድቡ የኢኮኖሚ መረጋጋትን ሲያረጋግጡ፣ ባንኮች ፋይናንስ ሲያደርጉና ባለሀብቶች ታጋሽ በመሆን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት ሲያሳዩ ትክክለኛው ለውጥ እውን እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡