በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽል መሠረት ተጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽል መሠረት ተጥሏል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉና አገሪቱን የሚያሻግሩ ዘላቂ የሆኑ መሠረቶች እየተጣሉ መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የ50 ዓመታት ጉዞን እንዲሁም የቀጣይ ሥራዎችን ትኩረት ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል፡፡
ከዛሬ መስከረም 19 እስከ 21 ቀን 2019 ዓ.ም በሚቆየው መርሃ-ግብር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር፣ የፈጠራና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች የማብሰር ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን፤ በዘርፉ የተከናወኑ የኢንተርፕረነርሽፕ ትግበራዎች፣ የተመዘገቡ ውጤቶችና ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት የተሰበሰቡ ዋና ዋና ስኬቶች በዝርዝር ይቀርባሉ።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence)፣ ሮቦቲክስና ስማርት ሲስተሞችን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ለጎብኚዎች ዕይታ ቀርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ሥርዓት፣ እንዲሁም ወደ ተደራጀና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር የተሸጋገረበት ውጤታማ ሥራ ተከናወኗል።
በዚህም አገራዊ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ17 ሚሊዮን ወደ 65 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተመዘገቡበት የ'ፋይዳ' ብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ እና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጆች መውጣታቸው የዲጂታል እምነት መሠረትን ያጠናከሩ አበይት እርምጃዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ግባችን ቴክኖሎጂን ከማላመድ አልፎ ወደ ውጭ ወደ መላክ ደረጃ መሸጋገር ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተልዕኳቸው ዲጂታል ሥርዓትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ምርምርንም ማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል።
የዲጂታል ሽግግሩን እውን ለማድረግና ለችግሮች ቁልፍ መፍትሔ የሆኑትን ስታርታፖች ለማገዝ የስታርታፕ አዋጅ ሥራ ላይ መዋሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም የቴክኖሎጂ ምህዳሩን ተረክቦ ለውጤታማነቱ የሚሰራ ትውልድ የማፍራት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ቴክኖሎጂን በጤና፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተግባራዊ የማድረግ ጅምሮች አበረታች ውጤት እየተገኘባቸው እንደሚገኝና ይህም የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽል መሠረት መጣሉን ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።