የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንሰራራት አንዱ አካል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንሰራራት አንዱ አካል ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የሚገነባው የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ማንሰራራት እውን የሚያደርግ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ አጋርነት የሚተገበር ነው።
ፕሮጀክቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ እንዲሁም የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አሊኮ ዳንጎቴ በተገኙበት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የሎጂስቲክስ ወጭንና መዘግየትን በመቀነስ፣ የኢነርጂ ዋስትናን ያጠናክራል፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የንግድ መስመርን ፍጥነትና ዘላቂነትን ያሳድጋል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ የኢትዮጵያን የኃይል ዋስትና ማሻሻል፣ ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ማሳደግ እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ማጓጓዝን ማረጋገጥ መሆኑም ተመላክቷል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተጣራ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው የነዳጅ አቅርቦት ሂደትን በማፋጠን በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ደሴ ክብረት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተሳሰር የምታከናውናቸው የልማትና የመሰረተ ልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው።
በመሆኑም መሰል ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ እያደጉ ላሉ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያነገቡ እና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ዝርጋታው የተጀመረው የተጣራ የነዳጅ ምርቶች ማጓጓዣ መስመሩ ቀደም ሲል ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ሂደት ላይ ይገጥሙ የነበሩ ውጣ ውረዶችን የሚያስቀር በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ማንሰራራት እውን ከማድረግ ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ እንዳለ ቱሪ በበኩላቸው፤ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ለዜጎች ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል ነዳጅ በተሽከርካሪ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ እና ጊዜ በመቀነስ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አስፋው ሽፈራው በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሚደረግ ጥረት ይወስድ የነበረውን ጊዜ እንደሚያሳጥርና ያለምንም የደህንነት ስጋት ማስገባት ያስችላል ነው ያሉት።
የተጣራ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቱ ከነዳጅ ባለፈ ሀገራቱ ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር አፍሪካውያን በትብብርና በጋራ ማደግ እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የነዳጅ አቅርቦትን በማቀላጠፍ ሀገር በብዙ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል ያሉት ደግሞ አቶ ነብዩ ከበደ ናቸው።