ቀጥታ፡

የኤልኒኖ ክስተት ተጽዕኖዎችን ለመከላከል መዘጋጀት ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦የኤልኒኖ ክስተት የሚያመጣቸውን መልካም እድሎች ለመጠቀምና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ። 

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኤልኒኖ ክስተት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ እየጠnነከረ ይሄዳል። 

ኤልኒኖ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች እንዲሁም በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የደቡብ አጋማሽ የሀገራችን ክፍሎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንዲኖር አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል። 

ከጥቅምት ጀምሮ የሚኖረው የዝናብ መጠንና ስርጭት በተለይም ለሱማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል፣ ለጉጂ፣ ለቦረና፣ ለሲዳማ እና ለደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። 

ይህም ዝናብ ከወዲሁ የመስኖ ስራዎችንና የተለያዩ የግብርና እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን፣ እንዲሁም ለአርብቶ አደሩና ለከፊል አርብቶ አደሩ የእንስሳት መኖ አቅርቦትን በማሻሻል በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት የምዕራብ ህንድ ውቅያኖስም በከፍተኛ ሁኔታ እየሞቀ ይገኛል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የኤልኒኖ ክስተት እና የህንድ ውቅያኖስ ሙቀት መጨመር በአንድ ጊዜ በሚጣመሩበት ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። 

በዚህም መሰረት ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ በምስራቅ አማራ፣ በምስራቅ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የመፈጠር እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ከመደበኛ በላይ በሚኖረውና ተደጋጋሚነት ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በዋቢ ሸበሌ እና በገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት እድሉ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህም በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ከወዲሁ በዋቢ ሸበሌ፣ በኦጋዴን እና በገናሌ ዳዋ አካባቢዎች የተቀናጀ የወንዝ አመራር ስርዓትን መተግበር አስፈላጊ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ 

በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከመደበኛ በላይ የሚኖረው የዝናብ መጠን ያለው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሊከሰቱ የሚችሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ለማህበረሰቡ ተደጋጋሚነት ያለው የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም