ቀጥታ፡

ኢንዱስትሪ:- የኢትዮጵያ ዘላቂ እድገት መሠረት

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ብልጽግና እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማረጋገጥ እንደ ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል ወስዶ እየሠራበት ይገኛል።

በኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ አማካኝነት የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ በላይ አድጓል።

ይህ ስትራቴጂካዊ ተግባር በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ከ1000 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ዳግም ወደ ማምረት እንዲመለሱ ያስቻለ ሲሆን፤ አጠቃላይ የዘርፉን ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔም የሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እያጠናከረ ይገኛል።

ኢንዱስትሪው ከሌሎች ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች፣ በተለይም ከግብርና እና ከማዕድ ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ሰፊ ስልታዊ እመርታዎችን አስመዝግቧል።

ስትራቴጂካዊ የሆኑ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ5.9 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የተገነቡት 10 አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችለዋል።

ወደ እነዚህ ፓርኮች ከገቡት አዳዲስ ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸው የሀገር በቀል አቅምን በመገንባትና ለሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በቀጣይም መንግሥት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማፅናት በ2018 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘውን ገቢ ወደ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማድረስ እቅድ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

ይህንን ታሪካዊ እቅድ ለማሳካት አዳዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እና የፋይናንስ አቅርቦቶችን ወደ ተግባር ማስገባት፣ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት እና ኢንዱስትሪዎችን በከተሞች ብቻ ከመወሰን ወጥቶ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች የሚያሰፋውን "የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን" ንቅናቄን መተግበር በቀጣይነት ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የዘይት ፋብሪካዎችን አቅም ማሳደግና የአነስተኛ አምራቾችን የክላስተር ማዕከላት ማስፋት የኢትዮጵያን ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር ስትራቴጂካዊ ፋይዳው የጎላ ነው።

See less

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም