ፕሮግራሙ የቁጠባና የስራ ባህላችንን በመቀየሩ ተጠቃሚ ሆነናል- የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮግራሙ የቁጠባና የስራ ባህላችንን በመቀየሩ ተጠቃሚ ሆነናል- የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች
ሀዋሳ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ) :- የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የቁጠባና የስራ ባህላቸውን በመቀየሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን በሀዋሳ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በ88 ከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ይገኛል።
በሐዋሳ ከተማ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችም፤ ፕሮግራሙ የቁጠባና የሥራ ባህላቸውን በመቀየር በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሲቲ ነሪ፤ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በችግር ከሚኖሩበት ሕይወት ተላቀው የተሻለ ገቢ በሚያገኙበት ሥራ እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
በአካባቢ ልማት ሥራ ተሳትፈው ከፕሮግራሙ የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ፍየልና በጎችን ገዝተው በማርባት የኑሮ ሁኔታቸውን እንደቀየሩ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር በመደራጀት መንግሥት ባዘጋጀላቸው የመሥሪያ ቦታ የሻይና ቡና ሥራ ላይ መሰማራታቸውንና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ፕሮግራሙ የቁጠባና የሥራ ባህላቸውን የሚቀይር የክህሎት ሥልጠና በማስገኘቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ለሦስት ዓመታት በተለያዩ የአካባቢ ልማት ሥራዎች መሳተፋቸውን ያስታወሱት ሌላኛው የፕሮግራሙ ተጠቃሚ አቶ ተሾመ ጫማ ናቸው።
በወቅቱ የሚያገኙትን ገንዘብ ቆጥበው የራሳቸውን ሥራ መጀመራቸውንና በአሁኑ ወቅትም ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆኑ የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ በመክፈት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማፍራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ጠቅሰው ለስምንት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የትምህርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ትውልድን እያነጸ ነው ያሉት ደግሞ በሐዋሳ ከተማ የንጋት ኮከብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አምሮት አስናቀ ናቸው።
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ የምግብ ዋስትና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ሃሚሶ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ ታቅፈው በአካባቢ ልማት ሥራ ተሳትፎ ያደረጉ ከ4 ሺህ 257 በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከተረጂነት ተላቀው በተለያዩ የሥራ መስኮች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንና ውጤታማ መሆናቸውን አብራርተዋል።