ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአዲሱ ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ መስከረም 22 ይካሄዳል

አሶሳ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤ መስከረም 22 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ገለጹ።

አፈ-ጉባዔዋ በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት፤ ጉባኤው የክልሉ መንግስት የሚመሰረትበትና አዲሶቹ የምክር ቤቱ አባላት የአምስት ዓመት ቆይታ ጊዜያቸውን ስራ የሚጀምሩበት ነው።

ዕለቱም በጉባኤው የሚመሠረተው አዲሱ የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የሚያስቀጥልና በክልሉ ሰላምን ለማጽናት የሚያስችል የህዝብ ኃላፊነት የሚረከብበት ነው ብለዋል።

ከጉባኤው ቀደም ብሎ ለአዲሶቹ የምክር ቤት አባላት ስለ ምክር ቤታዊ አሰራሮች፣ ተግባር እና ኃላፊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

አፈ-ጉባዔዋ የህዝብ ውክልናን በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ነባር የምክር ቤት አባላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም