ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ከተሞች ትንሣኤ ምልክት

የነገዋን አፍሪካ ብሩህ ተስፋ በጉልህ እያሳየች የምትገኘው አዲስ አበባ፣ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበች የምትገኘው አንጸባራቂ ለውጥ የአህጉራዊ ከተማ ልማት ፋና ወጊነቷን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው።

ይህ ሽግግር ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ሥልጣኔና ዕድገት አዲስ ተስፋን የፈነጠቀና ትንሣኤን የሚያበስር ተምሳሌት ሆኗል።

የከተማዋ ንፁህ የእግረኛ መንገዶች፣ ዘመናዊ የጎዳና ላይ መብራቶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማቶች አጠቃላዩ የአፍሪካ የትንሣኤ ሕልም ዕውን ሊሆን እንደሚችል በተግባር ያሳዩ ማረጋገጫዎች ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ ማዕከል የመሆኗን ያህል፣ አዲሱ ገጽታዋም የፖለቲካዊ እና የአንድነት መገለጫነቷን ይበልጥ አጉልቶታል።

የከተማዋ ጎዳናዎች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ስም የተሰየሙ መሆናቸው የአፍሪካን ብዝሃነትና ትስስር የሚያሳይ ሲሆን ይህም አዲስ አበባን የአፍሪካ የጋራ ማንነት እምብርት መሆኗን በፅኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት፣ ይህ የኮሪደር ልማት የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን የቦታ እና የጊዜ ምልከታን በመቀየር የትውልድ ሥነ ልቦና ስብራትን እያረቀ ያለ ታሪካዊ ሥራ ነው።

ይህ ራዕይን ወደ ተግባር የመቀየር ስትራቴጂ በተግባር የተገለጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል ማሳያ ሲሆን፣ ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለዘላቂ ትውልድ የሚሻገር አሻራ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ሽግግር ከውበት ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ እና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም ያሳደገ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያስገኘ ያለ ታላቅ ተግባር ነው።

ቀደም ሲል ለጎርፍ ተጋላጭና የቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ አረንጓዴ፣ ጤናማና ለነዋሪዎች ምቹ ስፍራዎች የተቀየሩ ሲሆን፣ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ ሁለገብ የገበያ ማዕከላትም የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ የበኩላቸውን ሚና እያበረከቱ ነው።

አዲስ አበባ በእግር ለመጓዝ ምቹ፣ አረንጓዴ እና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገች የአፍሪካ ከተሞች የለውጥ ምሳሌ መሆኗን በሀገራት መሪዎች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና በጎብኚዎች ተመስክሮላታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም