የሰውና የተፈጥሮ መልካም ትስስር ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
የሰውና የተፈጥሮ መልካም ትስስር ማሳያ
ጋምቤላ ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የሰውና የተፈጥሮ መልካም ትስስር ማሳያ
የጋምቤላ ክልል በሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ የውሃ ሀብት፣ ደኖች፣ የሣር ምድሩና በዱር እንስሳትና ብዝሃ ሕይወት እምቅ ሃብት ያለው መሆኑ ይታወቃል። የአኙዋሃና የማጃንግ የተፈጥሮ ሃብቶች ለልዩ የቱሪዝም መስህቦች ሆነው ይጠቀሳሉ።
በተለይም ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በሰፊ የሳር ሜዳዎች፣ በውሃ አካላትና በተለያዩ የዱር እንስሳት የበለፀገ የተፈጥሮ ሀብት ነው። የዱር እንስሳት ጉብኝት፣ የአዕዋፍ እይታ፣ የተፈጥሮ ጉዞና አጠቃላይ የኢኮ-ቱሪዝም ሃብት ፓርኩ የታደለ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወንዞችና ረግረጋማ መሬቶች፣ የደን ሃብት ከሰዎች አኗኗርና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ጋር በማሰናሰል የቱሪዝም ሃብት ማድረግ ተችሏል።
በመሆኑም ጋምቤላ ያለውን የተፈጥሮና የባህል እምቅ ሃብት በዘላቂነት በማልማት፣ የተፈጥሮ ጥበቃን ከቱሪዝም ልማት ጋር በማስተሳሰር ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት አዲስ አቅም መፍጠር እየተቻለ ነው።
የባዮስፌር ሪዘርቭ ዋና ዓላማ ተፈጥሮን ከሰው ልጅ የኢኮኖሚና የኑሮ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ የዘላቂ ልማትና የምርምር ከባቢን መፍጠር በመሆኑ በዚሁ መሰረትም የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ እና የማጃንግ የተፈጥሮ ደን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሊመዘገብ ችሏል።
የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሰፊ ምድር ያካለለ ሲሆን በውስጡ በርካታ የዱር እንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ።
በጥብቅ ደኑ ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ የዕፅዋት፣ ከ327 የሚልቁ የአእዋፍ፣ ከ86 በላይ አጥቢና ተሳቢ የእንስሳት ዝርያዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአኙዋሃ ባዮስፌር ሪዘርቭ የተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሳይሆን የሰውና ተፈጥሮ መልካም ትስስር ማሳያ፣ የዱር እንስሳት ሃብት ኮሪደር እና የዘላቂ ልማት ማዕከል ነው ማለት ይቻላል።
የአካባቢው ሕዝብ ከተፈጥሮው ጋር ተስማምቶ በመኖር የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅና ለትውልድ ጠብቆ በማቆየት ረገድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
በ225 ሺህ 490 ሄክታር ላይ የተንጣለለው የማጃንግ የተፈጥሮ ደንም በውስጡ 550 የዕፅዋት ዝርያዎች፣ 33 የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች እንዲሁም 130 የአእዋፍ ዝርያዎች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዝቅተኛና ከፍተኛ መልክአ ምድርን አካቶ የያዘው ጥብቅ የተፈጥሮ ሃብቱ በተለይም ለንብ ማነብና ለፍራፍሬ ልማት እጅግ ተመራጭ አካባቢ ነው።
የጋምቤላ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ለምግብ ዋስትና እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፉ ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።