ቀጥታ፡

የምክር ቤት አባላት የሕዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል

ባህር ዳር፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የምክር ቤት አባላት አሠራርን፣ ሕግንና ደንብን መሠረት በማድረግ የሕዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ አስገነዘቡ።

በተሻሻለው የአማራ ክልል ምክር ቤት አደረጃጀት፣ አሠራር፣ ሥነ-ሥርዓትና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ዙሪያ ለምክር ቤት አባላት የተዘጋጀ 7ተኛ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጀምሯል።


 

በወቅቱም የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በመድረኩ እንደገለጹት፤ የምክር ቤት አባላት በሕዝብ ዘንድ የተጣለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል። 

አባላቱ አሠራርን፣ ሕግንና ደንብን መሠረት በማድረግ የሕዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የሕዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አባላቱ በታማኝነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው፤ የአስፈጻሚውን አካል የልማት ዕቅዶች አተገባበር፣ ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ለውጤታማነቱ ይበልጥ መሥራት ይገባል ብለዋል።

አባላቱ ከግልና ቡድናዊ አስተሳሰብ በመውጣት ሕግና አሠራር ተፈጻሚ እንዲሆን በማድረግ፣ የሕዝብ መብት እንዲጠበቅና የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በታላቅ ኃላፊነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

የሥልጠናው ዓላማ የምክር ቤት አባላት በቀጣይ አምስት ዓመታት በሕዝብ ውክልናቸው ወቅት ሕግን፣ አሠራርንና የሥነ-ምግባር ደንቦችን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመድረኩ መካሄድ በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ዕውቅና በመፍጠር፣ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን ማካሄድ እንዲቻል ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በ7ተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የተመረጡ የምክር ቤቱ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም