አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ማከናወን እንደሚጠበቅበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ህዝቡ ይበጀኛል በማለት አብላጫ ድምጽ የሰጠው ብልፅግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወቃል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በየክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ያገኙባቸውን ድምጾች ማግኘታቸው እንዲሁ ተጠቅሷል፡፡
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ተወካይ ምክር ቤትም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ማግኘታቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሳታፊነቱ እና አካታችነቱ እያደገ መምጣቱን በተጨባጭ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ፍላጎት በምርጫ ካርዱ በመወሰን የአዲሱን መንግሥት መመስረት በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል።
ኢዜአ የፊታችን ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የሚመሰረተውን መንግስት በሚመለከት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኢሳ ሁሴን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ የሚያጠናክርና የወል ትርክት ግንባታ ላይ ይበልጥ የሚሰራ መንግስት ሊሆን እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ትዕግስት ገብረየስ የሚመሰረተው አዲስ መንግስት የሴቶችና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ለሚያረጋግጡ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን እንዲሁ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ተናግረው ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን ለመዋጋት መንግሥት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሀገር ልማትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን በትኩረት እንዲሰራ እና ገበያውን ለማረጋጋት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም የተናገሩት ገድሞ አቶ አያሌው መኮንን ናቸው፡፡