በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች በማር ምርት ስራ ላይ ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች በማር ምርት ስራ ላይ ተሰማርተዋል
ባህር ዳር ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በንብ ማነብና በማር ማምረት ስራ ላይ መሰማራታቸውን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በ2019 በጀት ዓመት ከ40 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
የቢሮው የንብ ሃብት ልማት ባለሙያ አቶ ሙሃመድ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለንብ ማነብ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ አርሶ አደሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆን በዘመናዊ፣ የሽግግርና ባህላዊ ቀፎ የንብ ሃብት የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አናቢዎች እየተሳተፉበት እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ በተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ በከተሞች ጭምር የማር ምርትን በጥራትና በብዛት ለማምረት የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም አስረድተዋል።
ለምርቱ ጥራትና መጠን እድገትም በክልሉ የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።
አሁን ላይ አናቢዎች የሚያካሂዱትን የማር ቆረጣ በጥራትና ከብክነት በጸዳ መልኩ እንዲያከናውኑ ባለሙያዎች የተጠናከረ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዊ ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የጅብአይታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ስለሺ አረጋ ፤ በጓሯቸው 175 በዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎች የተሞላ ንብ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከማር ምርት ሽያጭ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው በዘንድሮው ዓመት የተሻለ ገቢ ለማግኘት የማር ቆረጣ ስራ መጀመራቸውን አስረድተዋል።
በ2012 ዓ.ም ከስምንት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በንብ ማነብ ስራ ላይ መሰማራቱን የገለፀው ደግሞ በምስራቅ ጎጃም አዋባል ወረዳ የደመና ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ቁሜ የኔውድ ነው።
የአካባቢው መስተዳድር በሰጣቸው ሼድ ላይ በ35 ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎ የንብ ልማት ስራ በማከናወን ከስራ ጠባቂነት ተላቀው የራሳቸውን ገቢ ለማግኘት መቻላቸውን ነው የሚናገረው።
በተያዝው ዓመትም ጥራት ያለው ማር አምርተው ለገበያ ለማቅረብ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት ከ36 ሺህ ቶን በላይ ማር በመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ መቻሉን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።