ቀጥታ፡

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ እየተዘጋጀን ነው

ድሬደዋ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ የስነ ልቦናና የትምህርት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ተፈታኝ ተማሪዎች ተናገሩ።

ተማሪዎቹ የክረምቱን ወቅት በአዲሱ የትምህርት ዘመን የሚማሩትን የትምህርት ዓይነት በማጥናት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው ይህም በቀጣይ በሚወስዱት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።   

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሆኑት የቤተ ናታል ትምህርት ቤት ተማሪ ተስፋማሪያም ጎንፋ እና የድሬዳዋ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነፃነት አረጋዊ፤ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል የስነ-ልቦና እና የትምህርት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

ተፈታኝ ተማሪዎቹ፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት በመስጠት ላይ ሲሆኑ፤ መምህራንም በክረምት ወቅት የክለሳ ትምህርት በመስጠት እንዳገዟቸው ሁሉ አሁንም ከመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ውጪ እገዛቸው እንዳልተለያቸው ገልጸዋል።

የመድኃኔዓለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተፈታኝ ተማሪ ናርዶስ ሰለሞን፤ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በክረምት ወቅት ጊዜውን በትምህርት እና በጥናት ማሳለፉን ነው የተናገረው። 


 

በክረምቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የክለሳ ትምህርት መስጠታቸውና ልምዳቸውን ማካፈላቸው በስነ-ልቦና እና በትምህርት የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚረዳውም ተናግሯል።

የድሬዳዋ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ-መምህር በሐይሉ አሸናፊ በበኩላቸው ዘንድሮ ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከማሟላት ባሻገር፤ የመምህራንን የማስተማር ብቃትና ክህሎት የመገንባት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። 


 

በተጨማሪም ለ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የክለሳ መርሃ-ግብር፣ የኮምፒውተር ስልጠና እና ያለፉትን ዓመታት የፈተና ወረቀቶች መስራትን ያካተተ የማብቃት ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የመድኃኔዓለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ካሳሁን ኃይሉ፤ ባለፈው ዓመት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተመዘገበው ውጤት የተሻለ እንደነበር አስታውሰዋል። 


 

በትምህርት ሂደቱ ላይ ያሉትን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመገምገም፤ የዘንድሮ ተፈታኞች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የክለሳ እና የማካካሻ ትምህርቶችን የመስጠት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአስተዳደሩ የብሔራዊ ፈተና ውጤት መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል። 


 

ዘንድሮም ይህን ለውጥ በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከትምህርት ቢሮ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት አመራሮች ድረስ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ የመማር ማስተማር ሥራው ተጠናክሮ መጀመሩን ተናግረዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ከመስከረም 5/2019 ዓ.ም ጀምሮ በገጠርና በከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም