አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት የልማት ምህዳሩን በማስፋት በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት የልማት ምህዳሩን በማስፋት በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል-ምሁራን
ጅማ ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሀገሪቱን የልማት ምህዳር በማስፋት የተመዘገበውን እድገት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ አዲስ የመንግሥት ምሥረታ ዝግጅት ላይ ትገኛለች።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ሀገሪቱን በቀጣዮቹ ዓመታት የሚመራበትን አዳዲስ መዋቅሮችና የልማት አቅጣጫዎችን በመቅረፅ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የልሂቃንና የምሁራን ድምፅ ዋነኛ ግብዓት ይሆናል።
በዚህ ረገድ አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት የሕዝብን ጥያቄዎች በዋና ዋና አጀንዳነት በመቅረፅ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የሀገሪቱን የልማት ምህዳር በማስፋት በኩል በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሪያድ ዳውድ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የህዝብን ይሁንታ አግኝቶ የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ትኩረት በመስጠትና በመልካም አስተዳደር ላይ በመስራት የሀገሪቱን የልማት ሂደት ማስቀጠል ይገባዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ ፤ በቱሪዝም፣ በመሰረተ ልማትና በግብርና ዘርፎች ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን የሀገሪቱን የልማት አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ሪያድ (ዶ/ር) አመልክተዋል።
በተለይም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የስራ ዕድል መፍጠርና ግብርናን በማዘመን የምርት አቅምን ማሳደግ ቀጣይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋትና በውይይት ማመን እንዲሁም በዲፕሎማሲ መስክ የተመዘገበውን እድገት በበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ሪያድ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በተለየ ሁኔታ ከፍ ብሏል ያሉት ምሁሩ፤ ይህንን የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ለልማት የተቀመጠ ገደብ እንደሌለ የገለጹት ሪያድ(ዶ/ር) ሁሉም ዜጎች በልማት ሂደት በንቃት በመሳተፍና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማሳደግ ከመንግስት ጋር በመተባበር ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሞሲሳ፣ መንግስት የሀገሪቱን አንድነት በማጠናከርና ለህዝቡ ጥያቄዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ምላሽ በመስጠት ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሀገር አንድነትና ሰላምን ማጽናት፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና የሀገሪቱን የእድገትና የብልጽግና ጉዞ ማስቀጠል ከአዲሱ መንግስት የሚጠበቁ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማትና የእድገት ስራዎችን በማስቀጠል የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራርን በበለጠ በመከላከልና በመቀነስ የልማት ስራዎች ውጤታማነትን ማሳደግም ቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዜጎችም በሀገር ጉዳይ የጋራ ራዕይ በመያዝና ከመረጡት መንግስት ጎን በመቆም ለሀገር እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።