የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ጉባዔውን የፊታችን ዓርብ ያካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ጉባዔውን የፊታችን ዓርብ ያካሄዳል
ሀረር፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ጉባዔውን የፊታችን ዓርብ እንደሚያካሂድ የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ገዛኸኝ በቀለ ጉባኤውን በማስመልከት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ 7ኛው የሥራ ዘመን ጉባዔውን የፊታችን ዓርብ መስከረም 22 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ይጀምራል።
ይህም የክልሉ መንግሥት የሚመሰረትበት የመጀመሪያው ጉባዔ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጉባዔውም የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ እና ምክትል አፈ ጉባዔ እንደሚመረጥ ጠቅሰዋል።
ለቀጣይ አምስት ዓመታት ክልሉን የሚያስተዳድርና የሚመራ ርዕሰ መስተዳድር እንደሚመረጥም ተናግረዋል።
ጉባዔው የክልሉ መንግሥት የስራ አስፈፃሚ አካላት የሚደራጁበት መሆኑንም አመልክተዋል።
ከጉባኤው አንድ ቀን ቀደም ብሎም ለነባር የምክር ቤቱ አባላት የሽኝት መርሃ ግብር እንደሚከናወን አቶ ገዛኸኝ ጨምረው አስታውቀዋል።