ቀጥታ፡

በቢሾፍቱ የኢሬቻ በዓል እንግዶችን በላቀ ደረጃ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል

ቢሾፍቱ ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ በቢሾፍቱ የኢሬቻ በዓል እንግዶችን በላቀ ደረጃ ተቀብሎ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ።

በሰባት የተፈጥሮ ሀይቆቿ፣ በተዋቡ ተራሮቿና በምቹ የአየር ንብረቷ የምትታወቀው ቢሾፍቱ፣ ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ ከምንጊዜውም በላይ ትደምቃለች።

በተለይም የእንቁጣጣሽ፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ሲደርሱ ደግሞ የከተማዋ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች በሕዝብ አጀብና በደመቀ ባህላዊ ስነ-ስርዓት ተሞልተው ይበልጥ ያበራሉ።


 

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በኢሬቻ ማክበሪያው ሆራ አርሰዴ አካባቢ 'የአርሰዴ ቀዬ' በሚል ተሰይሞ የተገነባው ማዕከል፣ ህዝቡ ባህላዊ አልባሳትንና ምግቦችን በአንድ ቦታ እንዲያገኝ ማስቻሉን በመግለጽ የተከናወነው ስራ እጅግ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በ'አርሰዴ ቀዬ' ውስጥ ለኢሬቻ በዓል፣ ለጉብኝትም ሆነ ለመዝናናት ወደ ቢሾፍቱ የሚመጣ ማንኛውም እንግዳ የሚፈልጋቸውን ባህላዊ አልባሳት፣ ባህላዊ ምግቦችና ኪነ-ጥበባዊ ክዋኔዎችን በአንድ ማዕከል ማግኘት እንደሚችል ገልጸዋል።

ከቢሾፍቱ የኮሪደር ልማት ጋር ተጣጥሞ የተከናወነው የሐይቅ ዳርቻ ልማት፣ የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ያለ ምንም ውጥረትና መጨናነቅ በሰፊውና በምቹ ሁኔታ ተዝናንተው ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት ሆኖ መገንባቱን ከንቲባው ገልጸዋል።

ለኢሬቻ ታሰቦ የተገነባውና ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው የሆራ አርሰዴ አዳራሽ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ወደ ሃይቁ የሚወስዱ መንገዶች ዳርና ዳር በችግኞችና በአበቦች መድመቁን አንስተዋል።

ቢሾፍቱ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ባህሉን እሴትና ወጉን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ለማክበር የሚያስችሉ አስፈላጊ ዝግጅቶችን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቋንም ከንቲባው ገልጸዋል።


 

ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም  ለሚካሄደው ታላቁ የኢሬቻ ሩጫ  ጎዳናዎቿን ማዘጋጀቷንም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ኹነትም የቢሾፍቱን ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን በጎና ውብ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጉልቶ ለማሳየት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሐሳብ መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበር መሆኑን  የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት መግለጹ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረትም የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ መስከረም 23 እና 24 ቀን 2019 ዓ.ም በተከታታይ የሚከበር ይሆናል።

የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የህዝቦች አብሮነት የሚገለጽበት ታላቅ በዓል በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም