ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሴኔጋል፤ ተጠባቂው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ መርሐ ግብር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ)፦ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ሴኔጋልን ዛሬ በሜዳዋ የምትገጥምበት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።

በምድብ 10 የሚገኙት ሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በባህር ዳር ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ በምድብ 10 የመጀመሪያ ጨዋታ በሱዳን 1 ለ 0 ተሸንፏል።

በቀድሞው የፈረንሳይ እና አርሰናል ኮከብ ፓትሪክ ቪዬራ የሚመራው የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ግጥሚያው ከሞዛምቢክ ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ሶስት ጊዜ በውድድር ጨዋታዎች ላይ የተገናኙ ሲሆን ሴኔጋል ሶስቱንም ጨዋታዎች አሸንፋለች።




እ.አ.አ በ1965 በቱኒዚያ አስተናጋጅነት በተካሄደው አምስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በወቅቱ በምድብ ሁለት ባደረጉት ጨዋታ ሴኔጋል 5 ለ 1 አሸንፋለች።

ሉቺያኖ ቫሳሎ በወቅቱ የኢትዮጵያን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ ያሳረፈ ተጫዋች ነበር።

ሞሮኮ እ.አ.አ በ1998 ላሰናዳችው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እ.አ.አ በ1996 እና 1997 ባደረጓቸው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሴኔጋል 2 ለ 1 እና 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

ሁለቱ ሀገራት ከ29 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ መድረክ ዳግም ተገናኝተዋል።

ኤድዋርድ ሜንዲ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ኢስማይላ ሳር፣ ኒኮላስ ጃክሰን እና ኢሊማን ንዳዬ በሴኔጋል ስብስብ ውስጥ ከሚገኙ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።




ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴኔጋልን ለመርታት ትፋለማለች።

ዋልያዎቹ ለዛሬ ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በባህር ዳር ስታዲየም ያደረጉ ሲሆን ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በተመሳሳይ ትናንት ልምምዱን በባህር ዳር ስታዲየም አከናውኗል።

ሁለቱ ሀገራት በምድባቸው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።

በባህር ዳር ስታዲየም በርካታ የኢትዮጵያ ደጋፊዎችን በመገኘት ቡድኑን ያበረታታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ካሜሮናዊው ዊሊ ስቴፋን ንጋህ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በተያያዘም የምድቡ መሪ ሱዳን ከሞዛምቢክ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም