ቀጥታ፡

ታላቋ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር

ኢትዮጵያ በታሪክ ጥልቀት፣ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና በህዝብ ብዛት እጅግ ግዙፍ ሀገር ነች። የብዙ ዘመናት አውድ የፈተነው የነጻነት፣ የአብሮነት እና የከፍታ ታሪኳ በዓለማችን የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ሀገራት ቀዳሚዋ የአፍሪካ የኩራት አክሊል አድርጓታል። ይህ ታላቅ ህዝብ እና ሀገር ከትናንትናው አኩሪ ታሪኩ ተነስቶ ወደ ነገ የሚጓዘው ሁልጊዜም ትላልቅ ርዕዮችን በማለም እና በማሳካት ላይ ተመስርቶ ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት የገነባችው የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነቷም ለዛሬው ማንነቷ ታላቅ የሞራል እና የስነ-ልቦና ከፍታን ይሰጣታል።


ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ወቅት የማይቻሉ የሚመስሉ አበይት ሀገራዊ ርዕዮችን ነድፋ ወደ መሬት በማውረድ ረገድ አቻ የማይገኝላት ተሞክሮ አላት። ታላቅ ህዝብ ታላቅ ህልምን ይሻል፤ ያንን ህልም ወደ ተግባር የሚለውጥ ብርቱ የሰው ሃይልም ከጎኑ አሰልፏል። በውስጡ የያዘው የትዕግስት፣ የጽናት እና የድል አድራጊነት መንፈስም ሁልጊዜም ከፍ ወዳሉ ከፍታዎች እንድትሸጋገር አድርጓታል።


የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ትልቅ ርዕይ ወጥና ማሳካት የምትችልበት ሕያው እና ዋነኛው ማሳያ ነው። መላው ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በሀብቱ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ ተሳትፎ የገነባው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ "እንችላለን" የሚለውን የኢትዮጵያውያን የማይበገር መንፈስ በዓለም ፊት ያስመሰከረ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።


*****
የታላቅነት ጉዞ በጠንካራ ኢኮኖሚ እና በምግብ ዋስትና እውን መሆን ላይ የተመሰረተ ነው። ሀገሪቱ የዘመናትን የግብርና አሰራር በማሻሻል፣ ለም መሬቷን በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲሁም የምርትና የግብይት ሰንሰለቶችን በማቀናጀት ራሷን ለመቻል የምታደርጋቸው ጥረቶች የዚሁ ትልቅ ርዕይ ማጠንጠኛ ናቸው።

 
*****
ቴክኖሎጂንና የዲጂታል የበላይነትን የተቀዳጀ ትውልድ መገንባት ለነገ የሚተው አይደለም። ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂዋ፣ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት አህጉራዊ እና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነቷን በብቃት እያረጋገጠች ትገኛለች። ወጣቱ ትውልድ በቴክኖሎጂ ታጥቆ የነገውን ዓለም እንዲመራ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።


****
ለታላቅ ሀገር እና ህዝብ ሁለንተናዊ ዕድገት የባህር በር ባለቤትነት መሆን የረጅም ጊዜ የህላዌ እና የልማት ርዕይ ነው። ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ በቀጣናው እያደገ የሚገኝ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆኗ፣ እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም እና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ አጋርነቷን በማስቀጠሏ፤ የባህር በር ባለቤት የመሆን መብቷን በሰላማዊ፣ በንግድ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አጥርታ በመስራት ላይ ትገኛለች። ይህ የፍትህ ጥያቄ ህዝቧን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የኢኮኖሚ አድማሱን የሚያሰፋ እና የጂኦፖለቲካ ሚዛኑን የሚያስተካክል ብሩህ ሀገራዊ እውነታ ነው።


***
እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ርዕዮች እና ተግባራት የሚሰሩት ለነገይቱ የበለጸገችና የሰለጠነች ኢትዮጵያ ነው። የዛሬው ትጋት የነገዋን ታላቅ እና ብልጽግናዋ የተረጋገጠች ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት እውን እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም