ለብሔራዊ ጥቅም የተደመረ አቅም - ኢዜአ አማርኛ
ለብሔራዊ ጥቅም የተደመረ አቅም
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክ፣ የጸና ህብረት እና የደመቀ የጋራ እሴት ባለቤት የሆኑ ህዝቦች መኖሪያ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው ሂደት ውስጥ የመልክአ-ምድር፣ የባህል፣ የቋንቋና የእምነት ልዩነቶችን በጸጋ አቅፈው የሚኖሩ በመሆናቸው፣ አብሮነታቸው በጥልቅ የታሪክ መሰረት ላይ የተገነባ ነው።
ይህ የጥንት የአብሮነት ታሪክ በውጭ ኃይሎችና በውስጥ ፈተናዎች የተፈተነ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም ለሀገራቸው ብሔራዊ ህልውናና ክብር ሲመጣ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በማድረግ በአንድ ግንባር የሚቆሙ ድንቅ ህዝቦች ናቸው።
በሀገራቸው ሉአላዊነት ላይ የተቃጣን ማንኛውንም የወረራና የጥቃት ሙከራ በጋራ የመከቱበት ታሪክ፣ ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዋዕትነት ታሪካቸውን በወርቃማ ቀለም ያደመቀው የጸና ሀገራዊ ማንነታቸው ማረጋገጫ ነው። ለዚህ የማይበገር ሀገራዊ ህብረትና የአንድነት አቅም ህያው ምስክሩ ታላቁ የዓድዋ ድል ነው።
አድዋ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅና ከምዕራብ ተንቀሳቅሰው በታላቅ ብሔራዊ ወኔ የተሰባሰቡበትና የተደመሩበት ታሪካዊ ክስተት ነበር።
በወቅቱ በዘመናዊ መሳሪያ የተደራጀውንና የቁሳቁስ የበላይነት የነበረውን የወራሪው የጣሊያን ጦር፣ ኢትዮጵያውያን በሀገር ፍቅር ስሜት በጋራ በመመከትና በጀግንነት በመታገል አሸንፈውታል።
አድዋ የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት ሚስጥር ለዓለም ያበሰረ፣ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት ፋኖስ የሆነና በዚያም የጸናችና ያልተደፈረች ሀገር ለትውልድ ማሸጋገር የተቻለበት ታላቅ የታሪክ ማዕዘን ነው።
የቀደመው ትውልድ በደምና በአጥንቱ ጠብቆ ያቆያትን ሀገር የተረከበው የአሁኑ ትውልድ ደግሞ፣ የጀግኖች አባቶቹንና እናቶቹን ፈለግ በመከተል በዘመናዊው አውድ በመደመር እሳቤ ጥላ ስር ተሰባስቦ ታላላቅ ብሔራዊ ጥቅሞችን እያሳካ ይገኛል።
የመደመር እይታ ኢትዮጵያውያን ተበታትነው የቆዩትን አቅሞቻቸውን፣ እውቀታቸውንና ሀብታቸውን አስተባብረው ለሀገር እድገትና ከፍታ እንዲያውሉ በማድረግ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ፈጥሯል። በዚህም በረጅም ዘመናት ታሪካችን ውስጥ የማይታሰቡ የሚመሰሉ ድሎች በተግባር እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶች መካከል ኢትዮጵያን ከስንዴ ተመጽዋችነት ነጻ በማድረግ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ወደ ማድረግ ደረጃ ያሸጋገረው የግብርና ልማት ስኬት ዋነኛው ነው። ሀገራችን ለዘመናት ገጽታዋ ሆኖ የቆየውን የእርዳታ እጅ የመዘርጋት ታሪክ በመቀየር፣ ራሷን መመገብ እንደምትችል በተግባር አስመስክራለች።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ጥረት፣ እውቀትና የፋይናንስ አስተዋጽዖ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የዘመናችን የዓድዋ ድል ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ግድብ የኢትዮጵያውያንን ቁርጠኝነት፣ አቅምና የጋራ ራዕይ ለዓለም ያሳየ ትልቅ የልማት ማሳያ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎንም፣ ከተሞችን ምቹ፣ ጽዱና ዘመናዊ በማድረግ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ጭምር ተምሳሌትና የመስህብ ማዕከል እያደረጋት ይገኛል።
ይህን ፈጣንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀጠል ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ህጋዊና ኢኮኖሚያዊ መብቷ የሆነውን የባህር በር ጥያቄ በጽናትና በስልጣኔ መንገድ ይዛ ለሀገር ልማትና የወደፊት እድገት እየተሟገተች ትገኛለች።
የቀጣናውን የጋራ ብልጽግና በሚያረጋግጥ መልኩ ለባህር በርና ወደብ አማራጮች የምታደርገው ጥረት የሀገሪቱን የነገ ተስፋ የሚያበራ ነው።
በእርግጥ በዚህ የከፍታና የዕድገት ጉዞ ውስጥ የኢትዮጵያን ከፍታ የማይፈልጉ የውጭ ባዳዎች እና የነሱ መሳሪያ በመሆን ሀገርን ሰላም ለማደናቀፍ የሚሰሩ የውስጥ ባንዳዎች የሚፈጥሩት ሴራና መሰናክል ቀላል አይደለም።
ነገር ግን፣ ኢትዮጵያዊያን ታሪካዊ ጥንካሬያቸውን በመዘንጋት የሚበታተኑ ህዝቦች አይደሉም፤ ይልቁንም ፈተና በመጣ ቁጥር በተደመረ አቅማቸው በጋራ በመቆም፣ ፈተናዎችን ወደ አዲስ ዕድልና ጥንካሬ የመቀየር ልምዳቸውን አሁንም እየደገሙት ይገኛሉ።