ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት መሰረተ ልማት ተደራሽነት፤ የትውልድ ግንባታ መሰረት 

የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት የሕዝብን ጤና ከመጠበቅና ንቁ ትውልድን ከመቅረጽ ባለፈ ለስፖርታዊ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለአገራዊ ገጽታ ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በዘመናዊው ዓለም ስፖርት ከውድድርና መዝናኛነት ባሻገር የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የሚቀይር፣ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (GDP) የሚያሳድግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞተር ሆኗል።

የዓለም አቀፉ የስፖርት ኢንዱስትሪ ዓመታዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከሦስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ማለፉና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ስፖርት የመሠረተ ልማት፣ የቱሪዝም እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ መፍጠሪያ አንዱ መንገድ መሆኑን ያረጋግጣል።

የመደመር መንግሥት ይህን ታላቅ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሴክተሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የስፖርቱን ሴክተር በዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ለማጠናከርና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዕከላትን ለመገንባት በርካታ አበይትና ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ማህበራዊ እመርታ ለሀገር ግንባታ መርሀ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በስፖርቱ ዘርፍ በተለይም በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጥርጊያ ሜዳዎችን ጨምሮ 17,636 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።

👉የስታዲየሞች ዕድሳት እና ደረጃን የማሻሻል ሥራዎች

በአገሪቱ የተካሄደውን አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ በስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍ፣ በተለይም በስታዲየሞች ግንባታ፣ እድሳትና ዘመናዊ የማድረግ ሂደት በርካታ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ እንደሚሉትም፤ ከለውጡ በፊት የጥራት ችግሮችን ጨምሮ ስታዲየሞች ለታሰበው ዓላማ ያለማዋል ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። የመደመር መንግሥት ያመጣው መሠረታዊ የእይታና የምልከታ ለውጥ ግን ስታዲየሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በጥራት እንዲገነቡ ያስቻለ ሲሆን፣ በዚህም የሚደነቁ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን አንስተዋል።

ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ እና የአበበ ቢቂላ ስታዲየሞች ዓለም አቀፍ መስፈርት እንዲያሟሉ አጠቃላይ የከፍተኛ ደረጃ እድሳት ተደርጎላቸዋል። በተደረገላቸው ጥራቱን የጠበቀ ማሻሻያ የሐዋሳ እና ድሬዳዋ ስታዲየሞች የካፍ (CAF) ዕውቅና ማግኘት ችለዋል። የባህር ዳር ስታዲየምም የካፍን መስፈርት እንዲያሟላ ማድረግ ተችሏል። በዚህም ለአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ብቁ መሆን የቻለ ሲሆን ነገ ኢትዮጵያ ከሴኔጋል ጋር የምታካሂደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የሚያስተናግድ ይሆናል።

ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላና 62,000 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው የግዙፉ አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን የማፋጠን ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ የፊፋ (FIFA) ከፍተኛ ደረጃ፣ የአትሌቲክስ መለማመጃው ደግሞ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ (World Athletics) ከፍተኛ ደረጃ ዕውቅና ማግኘት ችለዋል።

👉የኮሪደር ልማት፤ ከከተማ ውበት ባሻገር

በአገራችን በተከናወኑት የከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎች አማካኝነት ማህበረሰብ አቀፍ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጋር አስተሳስሮ የመገንባት ተግባር በተለይም በአዲስ አበባ እና በክልል ዋና ዋና ከተሞች ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።

በልማቱ የተካተቱት ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መስመሮች እንዲሁም ክፍት የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎች የከተሞችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ከመቀየራቸው በተጨማሪ አሁን ላይ ዘመናዊ የስፖርትና የአካል ብቃት ማዘውተሪያዎች መሆን ችለዋል። እነዚህ መሠረተ ልማቶች ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በአካል ብቃት እንቅስቃሴና በጤናማ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲያሳልፉ በማድረግ ረገድ የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ለታዳጊዎች የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እጥረት ዋና ፈተና የነበረ ቢሆንም፣ የኮሪደር ልማቱ ግን ነፃና ተደራሽ የሆኑ ክፍት የስፖርት ስፍራዎችን፣ የስኬቲንግ ፓርኮችን፣ የቅርጫትና የሜዳ ኳስ ማዘውተሪያዎችን እውን አድርጓል። ይህም ታዳጊዎች ከታችኛው ዕድሜ ጀምሮ በሩጫ፣ በብስክሌትና በኳስ ጨዋታዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ለላቀ የስፖርት ስኬት እንደ መሰረት ድንጋይ እና ተሰጥኦ ማፍለቂያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት ዘመናዊ ማዘውተሪያዎች በሰፈሮችና በወጣቶች መካከል ማህበረሰብ አቀፍ ውድድሮች እንዲካሄዱ በማስቻል፣ የጤናማ ሕይወትና የውድድር ባህልን በስፋት ያዳብራሉ። በተመሳሳይ፣ በጥራት የተገነቡት የወንዝ ዳርቻዎችና የአረንጓዴ ስፖርት ስፍራዎች ኢትዮጵያ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ፌስቲቫሎች እንዲሁም ለስፖርት ቱሪዝም ያላትን የማስተናገድ አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።

ለዚህም ማሳያው በቅርቡ በአድዋ ድል መታሰቢያ ፕላዛ የተካሄደው የዓለም አቀፍ "ሲቲ ማውንቴን ባይክ" (City Mountain Bike) ውድድር ነው፤ ይህም ከተማችን የገነባቻቸው መሠረተ ልማቶች ለብስክሌትና ለአትሌቲክስ ስፖርቶች ብቻ ሳይሆን ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችም ምቹና ዋነኛ የስበት ማዕከል መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከረ ነው።

በአጠቃላይ፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ የሕብረተሰቡን የአካልና የአእምሮ ጤንነት የሚያንፁ፣ የወጣቶችን ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ የሚያወጡ እና ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የሚፈጥሩ ዘላቂ አገራዊ ሀብቶች ናቸው።

👉የስፖርት ማዘውተሪያዎች ግንባታ እና አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው

በኢትዮጵያ የስፖርት መሠረተ ልማት ማስፋፋት ከጤናና ማህበራዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አንቀሳቃሽ ኃይል እየሆነ መጥቷል። እየተከናወኑ ያሉ መሠረተ ልማት ግንባታዎች የከተሞችን የንግድ እንቅስቃሴ በማስፋፋት አዲስ የኢኮኖሚ ምህዳር በመፍጠር ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ሂደትም መንግሥት የመሠረተ ልማት አቅጣጫዎችንና መነሻ ግንባታዎችን ሲዘረጋ፣ የግል ዘርፉ ደግሞ ዘመናዊ አገልግሎቶችን፣ የንግድ ዕድሎችን እና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ሰፊ የሥራ ዕድል እያፈራ ይገኛል።

ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ግንባታ ገና ከመነሻው በግንባታው ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ማዕከላቱ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ሰፊ የንግድ ሰንሰለት ይዘረጋሉ። በአገልግሎት ዘርፉ ዘመናዊ የጂም (Gym) እና የስፖርት አካዳሚዎች እና ማሰልጠኛዎች በሰፊው እንዲስፋፉ መንገድ የተከፈተ ሲሆን፤ በችርቻሮ ንግድ በኩል ደግሞ የስፖርት አልባሳት፣ ቁሳቁሶች እንዲሁም የአካላዊ ብቃት ማሟያ ምርቶች ንግድ እንዲንቀሳቀስ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በስፖርት ማዕከላት ዙሪያ የሚከፈቱ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች እና የጤናማ ምግቦች መሸጫዎች የዕለት ተዕለት የገበያ ፍሰትን የጨመሩ ሲሆን፣ እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ መዝናኛዎች የትራንስፖርትና የመዝናኛ ዘርፉን ገቢ አሳድገውታል።

እነዚህ ስፍራዎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ፍሰትን በመጨመር የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲያድግ ያደረጉ ሲሆን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (በተለይም ወጣቶችና ሴቶች) በተለያዩ የፈጠራና አገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ አስችለዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችና የስፖርት ማዕከላት መገንባታቸው ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን፣ ጉባኤዎችንና የስፖርት ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። ይህም የውጭ አገር ስፖርተኞች፣ ደጋፊዎችና የጋዜጠኞች ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ የውጭ ምንዛሪ (Foreign Currency) የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ፣ የሆቴል፣ የኤርፖርት፣ የቱሪዝም ዘርፎች ከውድድሮቹ ሰፊ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያገኙ እያደረገም ይገኛል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በጥራት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶች ማዕከል እንዲሁም የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይም በርካታ ውድድሮችን የማስተናገድ ዕድል ያላት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ይህም ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማስገኘቱም በላይ ለገጽታ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2026 የአፍሪካ ባህል ስፖርት ፌስቲቫልን የምታዘጋጅ ሲሆን፣ በ2027 ደግሞ ከፍተኛ የወርቅ ደረጃ ያለውን የዓለም አትሌቲክስ ውድድርና የዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ኮንፈረንስን በበላይነት ታስተናግዳለች። እነዚህን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዘጋጀቷ የሀገሪቱን በጎ ገጽታ ከመገንባቱም በላይ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

በመደመር ፍልስፍና የተመራው የስፖርት ዘርፍ ሽግግር በአመለካከት፣ በፖሊሲ፣ በተቋማዊ አደረጃጀትና በአሠራር ላይ የተካሄደ ሙሉ ለውጥ ነው። ይህ አዲስ እይታ ስፖርትን ከመዝናኛና ከውድድር ባለፈ ለጤናማ ዜጎች ግንባታ፣ ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለሀገራዊ ትርክት፣ ለኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ገጽታ ግንባታ እንደ ዋና የልማት ምሶሶ እንዲያገለግል አድርጎታል። ለዚህ ሥርዓታዊ ሽግግርም የተከናወኑ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች፣ የስፖርት መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የማህበረሰብ ስፖርት ተሳትፎ ከ5.6 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማደጉ እና ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችንና ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟን ማሳደጓ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ናቸው።

በተለይም በዘርፉ የተከናወኑት ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የስታዲየሞች እድሳት ኢትዮጵያን ለስፖርት እንቅስቃሴዎች ምቹና ደረጃዋን የጠበቀች ያደረጓት ሲሆን፣ ለታዳጊ ስፖርተኞችም ሰፊ የማሰልጠኛ ዕድል ፈጥረዋል። ይህም በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች አዳዲስ ተተኪ ተሰጥኦዎችን ለማፍራትና ለብሔራዊ ቡድኖች ለማበርከት ጠንካራ መሠረት ጥሏል። በተጨማሪም የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ዝግጅቶች እና ዲጂታል አሠራሮች ሀገሪቱ እንደ አፍሪካ ዋንጫ (AFCON) ያሉ ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በብቃት የማስተናገድ አቅምና ዝግጁነት እንዳላት በመመስከር፣ የበጎ ገጽታ ግንባታዋን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ላይ ይገኛሉ።

በቀጣይም የተጀመሩ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በጥራት በማጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያን የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶች ማዕከል እንዲሁም የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም