ቀጥታ፡

ከሌማት እስከ መስኖ የስንዴ ልማት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ)፦ ከሌማት እስከ መስኖ የስንዴ ልማት

የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ በብዛት በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተውን የአመራረት ልምድ በመተው የበጋ መስኖ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ኢንሸቲቮች ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚቻልበት አሰራር ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። 

ከአፋር እስከ ጋምቤላ፤ ከሶማሌ እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች ክልሎችም ያልታረሱ ሰፋፊ መሬቶችን ወደ ምርት በማስገባት ምርታማነትን ማሳደግ የታቸለበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። 

ከመስኖ የስንዴ ልማት እስከ የሌማት ትሩፋት፣ ከቡና እስከ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የምርት ብዝሃንትን በማስፋትና ምርታማነትን በመጨመር ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ስኬታማ እየሆነም ይገኛል። 

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምርት ወቅት በዝናብ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በመስኖ በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል በተግባር ታይቷል።

የሌማት ትሩፋት ሀሳብ ግብርናን በአንድ ሰብል ላይ ከመመስረት ይልቅ የቤተሰብን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በእንስሳት እርባታ፣ የወተት ምርት፣ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ ስራ ስኬት የተመዘገበበት ሆኗል።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የቡና ልማትና ምርታማነትን ከአረንጓዴ ልማት ኢንሸቲቭ ጋር በማቆራኘት የቡና ምርትና የሚገኘውም ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። በሩዝና የሻይ ምርትም እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያዎች በርከት ያሉ ቢሆንም ግንባታው የተጠናቀቀውን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በግንባታ ላይ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከሀገርም የተሻገረ አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸው እንደሚሆኑ ይታመናል። 

የቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የጋዝ ምርት ልማት የኢትዮጵያ ብልጽግና ምልክቶች ናቸው።

የዲጂታል ልማት ስትራቴጂውና በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣው ውጤትም ሌላኛው የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያ ነው። የዲጂታል ሽግግሩ ትርጉም ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት አሠራርን፣ የንግድ ሂደትንና የዜጎችን ከአገልግሎትን ግልጽና ቀልጣፋ ማድረግን አላማ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም የመሶብ አንድ ማእከልን ጨምሮ ሌሎች የዲጅታል አገልግሎቶች እየተስፋፉና እየተለመዱ መጥተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ወደ ውጤት ለመቀየር አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ሁሉንም የልማት ኢንሸቲቮች በማሰናሰል ከህዝቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ለስኬት ማብቃት ይጠበቅበታል። 

የትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብና ታላቅ ርእይ  የሰነቀችው ሀገር በመንግስት ጥረትና በህዝቧቿ የተደመረ አቅም ያሰበችውን ከማሳካት የሚያሰናክላት አንዳችም ሃይል የለም። 

የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ምልክቶች ብርቱ ልጆቿ በመሆናቸው ለውጤታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራና በትብብር መስራት የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም