ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከር በቁርጠኝነት መስራቷን ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ኢነርጂና ንግድን ጨምሮ ቀጣናዊ ትስስርን በሚያጎልቡቱ ጉዳዮች ላይ በጽኑ ቁርጠኝነት መስራቷን እንደምትቀጥል የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ተካሄዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በስብሰባው ላይ በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።


 

ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላይ የኢትዮጵያን ቁልፍ የልማት ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን፤ በተለይም የኢትዮጵያና የጅቡቲ የነዳጅ ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት የኢነርጂ ደህንነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማስተላለፊያ ማህበር (EAPP) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ መሆኗን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባቱ ለቀጣናው ሀገራት ንጹህ እና አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የስብሰባው ዋነኛ ትኩረት በንግድ ምቹነት እና በቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስር ላይ ያተኮረ ነበር።

በዚህም መሠረት ሚኒስትሩ እ.አ.አ ሴፕቴምበር 2026 በአዲስ አበባ በተካሄደው የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተደረሱ ውሳኔዎችን፣ በተለይም የቀጣናውን የንግድ ምቹነት ለማሻሻል ኮሚቴ መቋቋሙን አድንቀዋል።

እንዲሁም የቀጣናውን የኢነርጂ ትስስር ሁኔታ ለመገምገም የተደረገውን ጥናት መልካም የሚባልና ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ጥሩ አፈጻጸም እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም የአየር ንብረት መዛባትና ሌሎች ችግሮች እየተባባሱ በመምጣታቸው፣ ቀጣናው ከድንገተኛ አደጋ ምላሽ ባለፈ የረጅም ጊዜ የአይበገሬነት አቅም እንዲገነባ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዚህ ረገድም በኢኒሼቲቩ ስር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ለዜጎች ዘላቂ ደህንነት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አንስተዋል።

የአረብ ባንክ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት (BADEA) አዲስ የኢኒሼቲቩ አጋር ሆኖ መቀላቀሉን በደስታ እንደሚቀበሉት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ መሰረተ ልማት ግንባታ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ንግድ በቀጣናው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ያነሳ ሲሆን ሀገራት በቀጣይነት በባለሙያ ደረጃ ውይይታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ስምምነት ላይ መድረሱን ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ 2019 የተቋቋመው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ (HoAI)፣ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማሳደግ እና የጋራ የልማት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እንደ ዋና መድረክ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም