በሳይንስና ቴክኖሎጂ ነገን የሚሰሩ ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ነገን የሚሰሩ ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ)፦ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድና ነገን የሚሰሩ ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ፤ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና ተማሪዎች በተገኙበት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤትን መርቀው ከፍተዋል።
ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሮቦቲክስ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ፋና ወጊ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤትም የታዳጊዎችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክህሎት በማጎልበት የዩኒቨርሲቲውንና የማህበረሰቡን ትብብር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ለዩኒቨርሲቲው የታዳጊዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የስቲም (STEM) ማዕከል ተደማሪ አቅም በመሆን፣ ትምህርት ቤቱ ለፈጠራና ለክህሎት ልማት መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት በፈጠራና በቴክኖሎጂ የበለጸገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት በሚያስችል ቤተ-ሙከራ እና በወሳኝ መሰረተ ልማቶች የተሟላ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድና ነገን የሚሰሩ ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መሠረተ ልማት እየተገነባ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው በአግባቡ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ለማድረግና ከማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመጠበቅ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ በበኩላቸው፤ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የትምህርት ቤትና የትምህርት ማህበረሰብ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤትም በሳይንስና በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ በማፍራት፣ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ገንቢ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው፤ የልዩ ሞዴልና የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ተተኪ ልሂቃንን በማፍራት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ትምህርት ቤትም ታዳጊ ተማሪዎች የሳይንስና የቴክኖሎጂ የንድፍና የተግባር ተኮር ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚያበለጽጉበት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ የዩኒቨርሲቲውና የማህበረሰብ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መሰረተ ልማት ነው ያሉት ደግሞ የማህበረሰብ ትምህርት ቤቱ ቦርድ ሰብሳቢና የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ደበበ ናቸው።
ትምህርት ቤቱ በ2019 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል ከ1 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ተናግረዋል።