ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ጉዞ፡ ከፈተናዎች ወደ አህጉራዊ አርአያነት እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና

መግቢያ፡-ጤና የአንድ ሀገር የልማት አቅምን ከሚወስኑ መሠረታዊ ዘርፎች አንዱ ነው። የሕዝብ ጤና ሲሻሻል የሥራ ኃይሉ ይጠናከራል፣ የሕፃናት የትምህርት ተሳትፎ ይሻሻላል፣ የቤተሰብ የጤና ወጪ ይቀንሳል፤ በአጠቃላይም የኢኮኖሚ ምርታማነትን ይደግፋል። 

ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት መንግሥት የጤናውን ዘርፍ ተደራሽነት ለማስፋት ጥረቶችን ቢያደርግም፣ በፖሊሲ አፈጻጸም እና በመዋቅራዊ አቅም ረገድ በርካታ መሠረታዊ ክፍተቶች ገጥመውት ነበር።

ድንገተኛ አደጋዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም ማነስ፡ የምርመራ እና የቴክኖሎጂ ጥገኝነት፡ የመሠረተ ልማት እና የግብዓት እጥረት እንዲሁም  የሰው ኃይል እጥረትና ስርጭት አለመመጣጠን በዘርፉ ይስተዋሉ ከነበሩ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።


 

አክሞ ማዳንን ከታካሚ ተኮር እንክብካቤ ጋር ያጣመረው ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የጤና ፖሊሲ፦

የመደመር መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት የሕዝብን ጤና በተሟላ መልኩ ለመጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ እና ዘመናዊ የጤና ፖሊሲ አቅጣጫን ተከትሏል። የፖሊሲው ዋና ማዕቀፍ መሠረታዊ ሕክምናዎችን ከማስፋፋት ባለፈ የጤና ሥርዓቱን በተቋማዊ፣ በሳይንሳዊና በቴክኖሎጂ አቅሞች ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። መንግሥት የጤና ደህንነትን ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በማያያዝ ስጋቶችን ቀድሞ መለየት፣ መከላከል እና በፍጥነት ምላሽ መስጠት የሚችል ጽኑ ሥርዓት መዘርጋት ችሏል።

በዚህ አጠቃላይ የጤና ማዕቀፍ ውስጥ አክሞ ማዳን እጅግ ወሳኝ ትኩረት ተሰጥቶታል። በሽታን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ጎን ለጎን፣ ቀደም ሲል ለታካሚዎች ፈታኝ የነበሩ የሕክምና ሂደቶችን ማዘመን፣ የታመሙ ዜጎችን በብቃትና በፍጥነት አክሞ የማዳን አቅምን ማጎልበት የፖሊሲው አንኳር አካል ሆኗል።

ለዚህም የሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት መስፋፋት፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገነቡት በርካታ ሆስፒታሎች እና የጤና ጣቢያዎች መሠረታዊ ሕክምናዎችን ከመስጠት ባለፈ፣ ለተለያዩ አጣዳፊ እና ውስብስብ ሕመምተኞች የዕለት ተዕለት የአክሞ ማዳን አገልግሎት ይሰጣሉ።


 

የላቦራቶሪና የሕክምና ግብዓቶች ማሻሻያ፡

ታካሚዎች ፈጣን እና ትክክለኛ ምርመራ አግኝተው በወቅቱ ህክምና እንዲጀምሩ የሚያስችል የሀገር ውስጥ የላቦራቶሪ አቅም በመገንባቱ፣ አክሞ የማዳን ሂደቱ ውጤታማነትና ፍጥነት በእጅጉ እንዲጨምር ተደርጓል።

የሰው ኃይል ልማትና የልዩ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ፦

የሰለጠኑ ሐኪሞች፣ የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች እና የጤና ባለሙያዎች አቅም በመጠናከሩ፣ በከፍተኛ ህመም ላይ ያሉ ዜጎችን ከሞት አደጋ ታድጎ ወደ ጤናማ ሕይወት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት አምጥቷል።

የበሽታ መከላከል፣ የክትባት ሥርዓት እና እናቶችና ሕፃናት ጤና፦

የጤና ሥርዓቱ ጥንካሬ የሚለካው ሕመምተኞችን ከማከም ባለፈ፣ ኅብረተሰቡን ከታቀዱና ከድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቀድሞ በመከላከል አቅም ጭምር ነው። በዚህ ረገድ የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለክትባት ሥርዓት፣ ለበሽታ መከላከል እንዲሁም ለእናቶችና ሕፃናት ጤና ልዩ ትኩረት በመስጠት ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግቧል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ያካተቱ የክትባት ዘመቻዎች፦

ተላላፊ በሽታዎችን ከወደፊቱ ትውልድ ለመከላከል በፖሊዮ እና በሌሎችም በሽታዎች ላይ የተካሄዱ ሰፊ አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ተደራሽ አድርገዋል። ይህም ሕፃናትን ከዕድገት እና ከከፍተኛ የጤና ስጋት ነፃ እንዲሆኑ አስችሏል።


 

የእናቶችና ሕፃናት ጤና ጥበቃ የተቀናጁ ሥራዎች፦

የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ በተዘረጉ የተሻሻሉ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ የዘርፉ ተጠቃሚነትና የደኅንነት መጠን ከፍ እንዲል ተደርጓል።ይህ ሁለገብ የመከላከል ሥርዓት ትውልድን በጤና ለማነፅ እና የነገውን ሀገር ተረካቢ ኃይል ጤናማ ሆኖ እንዲያድግ ለማድረግ ትልቅ መሠረት ሆኗል።

ድንገተኛ አደጋዎችን የመቆጣጠር አቅም ፦

የጤናው ዘርፉ ለውጥ በተለይ በድንገተኛ የጤና ስጋቶች ጊዜ በግልጽ ታይቷል። ኮቪድ-19ን ተከትሎ የላቦራቶሪና የድንገተኛ ምላሽ አቅሞች በፍጥነት እንዲስፋፉ ተደርጓል።

የማርበርግ ወረርሽኝ ቁጥጥር- በ2025 መጨረሻ ላይ የተከሰተውን የመጀመሪያውን የማርበርግ ወረርሽኝ መቆጣጠር መቻሉ የዘርፉን አቅም በተግባር አሳይቷል።

የብሔራዊና የክልል የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማዕከላት ተከፍተው፣ በጂንካ ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ተቋቁሞ፣ ወረርሽኙን መቆጣጠር ተችሏል።በዚህም ከዓለም ጤና ድርጅት ጭምር አድናቆት የተቸረ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን ዓለም አቀፍ ዕውቅና፦ የጤና ሥርዓቱ ጥንካሬ የሚለካው ከዕለት ተዕለት አገልግሎት ባለፈ፣ ድንገተኛ አደጋዎችና ወረርሽኞች ሲከሰቱ በሚሰጠው የፈጣንና አስተማማኝ ምላሽ አቅም ጭምር ነው።

በዚህ ረገድ በ2026 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የደረጃ አንድ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ የዘርፉን አዲስ ምዕራፍ ያበሰረ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።

ይህ ድል በአፍሪካ አህጉር ቀዳሚ መሆን፦

ኢትዮጵያ ይህንን የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን እውቅና ያገኘች በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያዋ ያደርጋታል።ይህም የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ብቃትና የደረሰበትን የላቀ የዕድገት ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰከረ ነው።

የጤና ሉዓላዊነትና የዝግጁነት ማሳያ፦

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅቱ እንደገለጹት፤ እውቅናው ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና የተለያዩ ወረርሽኞች ቀድሞ መዘጋጀት የጤና ሥርዓቱን ጽናት፣ ዘላቂነት እና የጤና ሉዓላዊነት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው።

ይህ ትልቅ ስኬት በአንድ ቀን የተገኘ ሳይሆን፤ በረጅም ጊዜ የተደረገ ጥብቅ ዝግጅት፣ ቀጣይነት ያለው የባለሙያዎች ልምምድና ጥንቃቄ የተሞላበት ምርጫ፣ እንዲሁም ከአጋር ተቋማት ጋር በተደረገ የተቀናጀ ሥራ የተገኘ የጋራ ድል መሆኑንም አንስተዋል።

የዲጂታል ጤና ሥርዓት ሽግግር፦

የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አስተዳደር ሥርዓትን ዲጂታል የማድረግ ሥራ ተጠናክሯል። መረጃን በዲጂታል መንገድ በፍጥነት መሰብሰብ፣ መተንተን እና ስጋቶችን ቀድሞ መለየት የሚያስችል አሠራር ዘርፉን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ አሸጋግሮታል።

የላቦራቶሪ አቅም እና የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥር፦

ከዚህ ቀደም ለምርመራ ወደ ውጭ ይላኩ የነበሩ ናሙናዎች አሁን በሀገር ውስጥ በፈጣን ሁኔታ መመርመር መቻላቸው ትልቅ ድል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በ2026 የዓለም ጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በመድኃኒትና ሕክምና መሣሪያዎች ቁጥጥር ላይ ያላቸውን ትብብር ማጠናከራቸው የሕክምና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት አስተማማኝ አድርጎታል።

ማጠቃለያ፦ ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የታየው ለውጥ በጤና ተቋማት ቁጥር መጨመር ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከላይ የተዘረዘሩት የሰው ኃይል፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የድንገተኛ ምላሽ፣ የላቦራቶሪ እና የክትባት ሥርዓቶች በአንድ ላይ መጎልበታቸው፤ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ችግር ሲፈጠር ብቻ ምላሽ ከሚሰጥ አሠራር ወጥቶ ስጋትን ቀድሞ መለየት፣ መከላከል እና በፍጥነት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጽኑ የጤና ደህንነት ሥርዓት እየገነባ መምጣቱን በግልጽ ያሳያል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም