የነገን ትውልድ የዋጀ ልማት-የሕፃናት ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ - ኢዜአ አማርኛ
የነገን ትውልድ የዋጀ ልማት-የሕፃናት ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና እና ቀጣይነት የሚረጋገጠው በአካልና በአእምሮው የበለጸገ፣ በስነ-ምግባር የታነጸ እና ንቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ሲገነባ ነው።
ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ርዕይ ከግብ ለማድረስ ደግሞ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያላቸው ሚና እጅግ የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን እውነታ በመገንዘብ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋትንና ዘመናዊ ማዘውተሪያዎችን መገንባትን የትውልድ ግንባታ ስትራቴጂው ዋነኛ አካል አድርጎ በልዩ ትኩረት እየሰራበት ይገኛል።
መንግስት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም በየክልሉ እና በከተማ አስተዳደሮች በኩል በርካታ በጀት በመመደብ ሰፊ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታን አከናውኗል።
በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሁለገብ የወጣቶችና ስፖርት ማዕከላት እንዲሁም የህፃናት መጫወቻ ፓርኮች ተገንብተዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ህፃናትና ታዳጊዎች የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በቅርብ ርቀት እንዲያገኙ አድርጓል።
ይህ የመንግስት ስራ ታዳጊዎች ካሉበት የመኖሪያ አካባቢ ሳይርቁ በሰፈራቸው ውስጥ በሚገኙ ማዕከላት የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ሁሉም ህጻናት እኩል የስፖርት እና የመዝናናት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ማህበራዊ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ መንግስት ስፖርትን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማጠናከር በወሰደው እርምጃ በአዲሱ የትምህርት ካሪኩለም መሰረት ደረጃቸውን የጠበቁ የሜዳ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የቮሊቦል እና የሩጫ ትራኮችን በትምህርት ተቋማት ውስጥ ገንብቷል።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚደረጉ የስፖርት ውድድሮች እና ፌስቲቫሎች ህጻናት በትምህርታቸው ጎን ለጎን የአካል ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል።
ይህ አካሄድ ስፖርት እና ትምህርትን በተቀናጀ መልኩ በማስኬድ የተሟላ ስብዕና ያለው ዜጋ ለመቅረጽ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው።
እነዚህ ማዘውተሪያዎች ለታዳጊዎች ሁለንተናዊ የአካልና የአእምሮ እድገት የሚሰጡት ጥቅም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ከልጅነት ጀምሮ በስፖርት መሳተፍ ለአካል ጥንካሬ እና ጤናን ለመጠበ ይረዳል።በአዕምሮ ረገድም ህጻናት የራስ መተማመናቸውን እንዲያሳድጉ እና የአዕምሮ ንቃታቸውን በመጨመር በትምህርታቸው የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያደርጋቸዋል።
ማህበራዊ ፋይዳውን ስንመለከት፣ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ህፃናትን ከአልባሌ ቦታዎች እና ከተለያዩ ጎጂ ሱሶች በመታደግ ረገድ ወሳኝ ናቸው።
ታዳጊዎች ትርፍ ጊዜያቸውን በበጎ ተግባር እንዲያሳልፉ በማድረግ የስነ-ምግባርና የዲሲፕሊን ባለቤት እንዲሆኑ ያግዛቸዋል። እንደ እግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ባሉ የቡድን ስፖርቶች ውስጥ በመሳተፍም አብሮ የመስራትን፣ የጋራ ግብን ማሳካትን፣ መከባበርን እና መቻቻልን እንዲለምዱ ያስችላል።
በመንግስት የሚደገፉ የታዳጊዎች ስፖርት አካዳሚዎች እና የፕሮጀክት ማዕከላት መቋቋማቸው ደግሞ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ህጻናት በሳይንሳዊ መንገድ ለማሰልጠን አስችሏል።
እነዚህ ማዕከላት ሀገርን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያስጠሩ፣ የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ተተኪ ሻምፒዮኖችን ለማፍራት ትልቅ መሰረት ናቸው።
መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የማዘውተሪያ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከወቅታዊ ጠቀሜታቸው ባለፈ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት መሰረት የጣሉ ናቸው።
ስፖርት ሰዎችን ከልዩነት አውጥቶ በአንድነት ስለሚያቆም፣ ህጻናት ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ አብሮነትን እንዲለምዱ ያደርጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንዳሉት፤ የሰው ልጅ ስብዕና የሚቀረጸው በማኅበራዊ ግንኙነት፣ እርስ በርስ በመተሳሰብ እና በጤናማ ውድድር ነው። በዚህ ረገድም ማዘውተሪያዎች የአካል ብቃት ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆኑ የሀገር አንድነትና የትውልድ ጽናት የሚገነባባቸው ስፍራዎች ናቸው።
በመሆኑም እነዚህን የመንግስት ስራዎች ይበልጥ ሲጠናከሩ ጤናማ፣ ብቁ እና የነገዋን ጠንካራ ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ የሚገነባ ትውልድ ማፍራት ይቻላል።