ከአህጉራዊ መሪነት እስከ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መገለጫ - ኢዜአ አማርኛ
ከአህጉራዊ መሪነት እስከ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መገለጫ
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ፣ አህጉራዊ መሪነትን እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
የመደመር ፍልስፍና መሠረት ያደረገ አቅጣጫ፣ የውጭ ፖሊሲዋን ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት አሸጋግሮታል።
ይህ አዲስ የዲፕሎማሲ ጉዞ በዋናነት በአህጉራዊ ምሰሶነት፣ በባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ፣ በጠንካራ የሀገር ውስጥ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና በዜጋ-ተኮር አጀንዳዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርበው ታዳሽ ኃይል የውሃ ፖለቲካ ተጽእኖን በመስበር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማጠናከር ችሏል።
ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስከበር የባህር በር መኖር አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ይህንን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ ለማሳካት እየሰራች መሆኗን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች በስፋት እያንጸባረቀች ትገኛለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል ሚዛኑ እየተቀያየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የኃያላንና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ስብስብ በሆነው የብሪክስ ጥምረት ውስጥ ሙሉ አባል መሆን መቻሏ የዲፕሎማሲ አቅሟን ወደ ላቀ የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ይህ ስኬት ከዓለም መሪ ኢኮኖሚዎች ጋር እኩል የመደራደር አቅም የፈጠረላት ሲሆን፣ ለደቡባዊው ንፍቀ ዓለም (Global South) ፍትሃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ግንባታ ጥሪ በግንባር ቀደምትነት እንድትሟገት አድርጓታል።
በተጨማሪም ከእ.አ.አ 2025 እስከ 2027 ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧና በዓለም አቀፍ ተቋማት ያላት አመራር ሀገሪቱ ያላትን ተሰሚነት በግልጽ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ይበልጥ ጎልቶ የታየበት ሌላኛው ጉዳይ ሀገሪቱ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ መመረጧ ነው።
በዚህም የአፍሪካ ሀገራትን ሙሉ ድጋፍ ማግኘት ችላለች።
ይህ ትልቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ወደ አፍሪካ መመለሱ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በዓለም መድረክ ተቀባይነት ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ፣ አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድር እና የውሳኔ ሰጪነት ማዕከል አድርጓታል።
ይህ ስኬታማ የውጭ ዲፕሎማሲ የተገነባው በሀገር ውስጥ በተከናወኑ ጠንካራ ሁለንተናዊ ሪፎርሞች እና ዜጋ-ተኮር አስተሳሰቦች ላይ ነው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ከቀጣናዊ ምሰሶነት ወደ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የተሸጋገረበት ሁለንተናዊ የከፍታ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ይህ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በአረንጓዴ ልማት እና በዜጋ-ተኮር መርሆዎች ላይ የተገነባው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አካሄድ፣ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ ቀዳሚ አጀንዳ ቀራጭነት ያሻገረ እና የአህጉሪቱን ድምፅ የሚያስተጋባ ዘላቂ የአካሄድ ስልት ነው።