በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን ግሪሳ ወፍ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን ግሪሳ ወፍ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ደብረ ብርሃን፤ መስከረም 18 / 2019 (ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተውን ሰብል አውዳሚ የግሪሳ ወፍ መንጋ ለማጥፋትና ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ፡፡
በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ አፈወርቅ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግሪሳ ወፍ መንጋው በዞኑ በሚገኙ የአንፆኪያ ገምዛ፣ ኤፍራታና ግድም፣ ቀወት፣ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳዎች እና በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ተከስቷል።
የተከሰተው የግሪሳ ወፍ መንጋ በ140 ሺሕ 16 ሄክታር መሬት ላይ በሚገኝ የማሽላ፣ ጤፍ፣ ማሾና ሌሎች ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት በጥናት በተለዩና የመንጋው ማደሪያ በሆኑ 237 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኬሚካል ርጭቱን በቅርብ ሆኖ ለማከናወንም በሸዋሮቢት ከተማ ጊዜያዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስገንዝበዋል።
በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችም ጅራፍ ማጮህን ጨምሮ የተለያዩ የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም የግሪሳ ወፉን የመከላከል ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
ሌሎች አጎራባች ወረዳዎችም የተጠናከረ የሰብል አሰሳና ቅኝት በማካሄድ አዲስ ክስተት ሲኖር ፈጥነው በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የግብርና ጽሕፈት ቤቶችና ባለሙያዎች እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት ላይ 20 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደሚገኝ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።