በሲዳማ ክልል ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፣ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራርና የድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የሲዳማ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራርና የድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከ350 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ የለማውን የበቆሎ ምርት በኮምባይነር በመታገዝ እየሰበሰበ ነው።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ሃይሉ ሀሰና ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎችን ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
በዚህም በክልሉ በተለዩ አምስት ቦታዎች ላይ ከ350 ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት እህል የማከማቸት፣ ፈንድ የማሰባሰብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የመግዛትና የማህበረሰቡን የመረዳዳት እሴቶች የማጠናከር ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት በፌደራል መንግሥቱ የተቀመጠውንና ክልል አቀፉን ከ23 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የእለት ደራሽ እህል የማከማቸት እቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በ2018/19 በልግ ወቅት ከለማው 350 ሄክታር ማሳ ላይ የበቆሎ ምርት በኮምባይነር ታግዞ እየተሰበሰበ ሲሆን፣ እስከ 20 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር እህልና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ሥራው ውጤታማ መሆኑንም አብራርተዋል።
ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እህል የማከማቸት፣ የሰብል ልማትና የመጠባበቂያ ፈንድ ከማሰባሰብ በተጨማሪ የማህበረሰቡን የመረዳዳት እሴት የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሲዳማ "ፎጮ" በተሰኘ ባህላዊ ሥርዓት አማካይነት "ያለው ለሌለው" እህል የማሰባሰብ ተግባሩን በማስቀጠል፣ በሀገር በቀል እውቀት እርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የመጠባበቂያ ፈንድ መኖሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ በ2019 በጀት ዓመት መጨረሻ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ፈንድ ለማሰባሰብ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የወንዝ ሙላት፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ያስከተሉትን አደጋዎች በራስ አቅም መሸፈን እንደተቻለ ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ በቀጣይም ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መገንባቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲና ከፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሚገኙ መረጃዎችን መሠረት ያደረጉ ሳምንታዊ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።