ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን ማስፋት ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፤መስከረም 18/2019(ኢዜአ)፦ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡና ዕድገትን የሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎችን ማስፋፋት እንደሚጠበቅበት አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡  

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በገለጸው ውጤት መሰረት ህዝቡ ይበጀኛል ይጠቅመኛል በማለት አብላጫ ድምጽ የሰጠው ብልፅግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ይሁንታ ማግኘቱን ማሳወቁ ይታወቃል፡፡ 

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የክልሎች ምክር ቤቶችን መቀመጫ እንዲያገኙ ድምጽ ሰጥቷቸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ፍላጎት በምርጫ ካርዱ በመወሰን የአዲሱን መንግሥት መመስረት በጉጉት እየጠበቀ ነው።

የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጹ ይታወቃል።

የፊታችን መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ከሚመሰረተው መንግስት ጋር በተገናኘ ኢዜአ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ከበደ ወዬቻ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት ዜጎች ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አንፃር ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ማሳደግ ላይ እና ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ማፋጠን ላይ አዲሱ መንግሥት ጠንካራ ስራ ያከናውናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመፈፀም አቅም እንዳላት አሳይቶናል ያሉት አስተያየት ሰጪው አዲሱ መንግሥት የተጀመሩ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ላይ አበክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ አልማዝ ሰቦቃ ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች በውጤታማነት መከናወናቸውን እንደተመለከቱ ጠቁመዋል።

በተለይም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ሲሰሩ የነበሩ ውጤታማ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ስራ መስራት ላይ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥልበታል ብለው እንደሚጠብቁም አክለዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መላክ ጌታነህ በበኩላቸው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህገ-መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት በመጠቀም በንቃት መሳተፋቸውን አውስተዋል።

ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገር የሚመራው አዲሱ መንግስት ህዝብን በማስተባበር ሀገር የሚጠቅም ስራ ለመስራት የገባውን ቃል በተግባር ያሳያል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች በውጤታማነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያረጋግጡ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያፋጥኑ የልማት ስራዎች በስፋት ተከናውነው ያየንበት ዘመን ላይ እንገኛለን ያሉት ደግሞ አለሚቱ ትዕዛዙ ናቸው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ባለፉት ዓመታት መመልከታቸውን ጠቁመው፣ ይህን ቁርጠኝነት አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያላቸውን ተስፋ አጋርተዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ግዛቸው ወልዴ በበኩላቸው አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የኢትዮጵያን ምጣኔ-ሀብታዊ ዕድገት ለማሳለጥ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን ይከተላል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ከፊታችን ባሉ ዓመታት አዲሱ መንግስት የኃይል አቅርቦትን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የሚበቁበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።


 

አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ለዓለም ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ይሉሻል ታደሰ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።

በቀጣይም መንግሥት የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸውን መስኮች በማስፋት ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም