የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለጨዎታዎች ዝግጁ መሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለጨዎታዎች ዝግጁ መሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አቅም የሚፈጥር ነው
ደሴ፤ መስከረም 19/2019 (ኢዜአ) -የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለጨዋታዎች ዝግጁ መሆን የቱሪዝም ዘርፉን በላቀ ደረጃ ለማነቃቃት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስታዲየሙ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች መሠረት በማድረግ ሲገነባ ቆይቷል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድቦ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትም ስታዲየሙ የካፍ እና የፊፋን መስፈርቶች አሟልቶ በመገኘቱ ጨዋታዎችን ማካሄድ የሚያስችል ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።
ስታዲየሙ ሥራ መጀመሩ የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባለፈ በዘርፉ ኢትዮጵያ የነበራትን ዝና መመለስ የሚያስችል መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
የስታዲየሙ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካና የአውሮፓ ክለቦችም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶች እንደተሟሉለት ጠቁመዋል።
በተለይም በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ታላላቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ተጫዋቾች በመኖራቸው የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በነገው እለት የሚደረገው ጨዋታ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ እንዲሳካ ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን የእግር ኳስ ቀደምት ታሪክ ለመመለስና ውጤቱን ለማሻሻል የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራትና የአካባቢውን ቱሪዝም በማነቃቃት ረገድም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ምክትል የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
ለውድድሩ የሚመጡ እንግዶችን የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴት በሚያስተዋውቅ መልኩ ለመቀበል ከሆቴሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት መደረጉንም ነው የጠቀሱት።
በውድድሩ ዕለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የድል ባለቤት እንዲሆን በማበረታታት እና በመደገፍ የስፖርቱ ቤተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።