ህዝቡ የሰጠንን ትልቅ አደራ ከግብ ለማድረስና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሰራለን - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ የሰጠንን ትልቅ አደራ ከግብ ለማድረስና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሰራለን - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዳማ ፤ መስከረም 18/2019(ኢዜአ )፦ ሕዝቡ የሰጠንን ትልቅ አደራ ከግብ ለማድረስና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሠራለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ጨፌ ኦሮሚያ የ7ኛው የጨፌ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አቶ ሽመልስ ለጨፌው ባሰሙት ንግግር ሁለንተናዊ እድገትን በማስመዝገብ የሕዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል።
የተገኘውን ድል መጠበቅ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ድሉን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠን መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከፊታችን ያሉት ማነቆዎች ፈታኝ ናቸው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ምርጫችን ሰላምና የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ልማትና ዕድገትን በማረጋገጥ ብልጽግናን እውን ማድረግ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ የሰጠንን አደራ ከዳር ለማድረስ የሕዝቡን ኑሮ ከመሠረቱ የሚያሻሽል ጠንካራ አሠራርና መዋቅር እውን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት፣ የጤና፣ አገልግሎትን በማዘመን፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ከተሞች ወሳኝ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የተቀናጀ መሠረተ ልማት የመዘርጋት ጅምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪና ግብርናን ማስተሳሰር፣ በገጠርና በከተማ መካከል ገበያና ምርትን ማስተሳሰር፣ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከድህነት ለመላቀቅ እንረባረባለን ብለዋል።
በቀጣይ ራስን በመቻል ዕቅድ ውጤታማ የሆኑ፣ የሕዝቡን ኑሮ ከመሠረቱ የሚያሻሽሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች በትኩረት ይቀጥላሉ ብለዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሙሉ አቅም እንሠራለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በየዓመቱ በአማካይ የ12 ነጥብ 5 በመቶ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ግብ መቀመጡን ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪ የክልሉ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሞተር እንዲሆን ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ግብ መቀመጡንም አብራርተዋል።
በዚህም ኢንተርፕራይዞችና በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ልማት ትስስርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመሬት አቅርቦት፣ ኢንቨስትመንትና ተወዳዳሪ የሆነ ምርትን ማሳደግ ትኩረት የተሰጣቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ ሽግግሩን ለማፋጠን የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ በተለይም ጥራት ያለው የኃይል፣ የቴሌኮምና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ማቅረብ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ምርቶችን የእሴት ሰንሰለት በመጨመር የኤክስፖርት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንሠራለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የቱሪዝም መስኮች በክልሉ ወሳኝ የገቢና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታት የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የገቢ አቅምን ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ለዚህም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማዘመንና ሀብትን ከብክነት በፀዳ መልኩ ማስተዳደር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አብራርተዋል።
የአርብቶ አደሩንና አርሶ አደሩን ሕይወት ከመሠረቱ ለመለወጥ የ'ሀሮሜ' ሞዴል መንደር ልማት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህም ፋይናንስን ጨምሮ የተሟላ መሠረተ ልማትና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራና የመንግሥት አገልግሎትን የማዘመንና ዲጂታል የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ አያይዘውም፤ ይህንኑ ሽግግር ለማሳካት አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ቀዳሚ ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል።