ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት ጽኑ መሰረት ላይ የቆመ ፍትሐዊ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የቀጣናውን ደኅንነት፣ ልማትና ብልፅግና የሚያፋጥን ፍትሐዊ አጀንዳ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።

ግብጽ ኢትዮጵያን ከሁለቱ ውሃዎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለመነጠል የምታደርገው ተደጋጋሚ ሙከራ እንደማይሳካ ከትናንት ታሪኳ መማር እንዳለባትም አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትና ተደራሽነት ጥያቄ መሰረታዊ፣ የብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሕልውና ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ለሶስት አስርት ዓመታት በባዕዳን ሴራ፣ በሀገር ውስጥ ተላላኪዎች ከሉዓላዊ የባሕር ዳርቻዋ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ መገፋቷን አስታውሰዋል።

በሀገር ላይ ከተፈጸመው የመልክዓ ምድራዊ እስረኝነት በደል ባሻገር፣ ጉዳዩን ማንሳት ለዓመታት መለያ የሚያስለጥፍ ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን እግር ከወርች የመልክዓ ምድራዊ እስረኛ የሚያደርገው ይህ ሁኔታ ሊታረም እንደሚገባው ገልጸው፤ ጥያቄው ሕጋዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ተደራሽነት ጥያቄም በጋራ ተጠቃሚነት ጽኑ መሰረት ላይ የቆመ ፍትሐዊ አጀንዳ ነው ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት፣ ልማትና ብልፅግና የማፋጠን እንደሆነ አስረድተዋል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚሳለጥባት ግዙፍ ሀገር የባሕር በር ተዘግቶባት የምትኖር እንዳልሆነችም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ከሞተበት ነፍስ በዘሩበት ማግስት በተሰራ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ የጥያቄውን ፍትሐዊነት ዓለም መገንዘቡን አስታውቀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የባሕር ላይ ደኅንነትን የማረጋገጥ ሙሉ መብት እንዳላትም ከታሪክ፣ ሕግ፣ መልክዓ ምድር፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት አኳያ ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም እንዴት ተግባራዊ ይሁን፤ እንዴትስ ምላሽ እንስጥ ወደሚል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ተሸጋግሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አቋም ግልፅ ነው ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ለዚህም ሁሉንም አሸናፊና ጋራ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መመለስ ይቻላል በሚል አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል።

ግብጽ ኢትዮጵያ የምታመነጨውን የ86 በመቶ የዓባይ ውሃ እየተጠቀመች ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄዋን ለማሳነስ የምታደርገው ጥረትም ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የሸረበችው ሴራ ተቀጥያ ነው ብለዋል።

ይህም ሀገሪቷ በምስራቅ አፍሪካ የምታራምደው አካሄድም ሳይሆኑ የመሆን ቀጣናዊ የአራጊ ፈጣሪነት ዝንባሌና ከዕውቀት ማነስ የሚመነጭ ክፍተት መሆኑን አንስተዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖም አንዳንድ የግብጽ ባለስልጣናትና ግለሰቦች የኢትዮጵያን የዕድገትና የብልፅግና የማንሰራራት ጉዞ እንደስጋት እንደሚቆጥሩት አንስተዋል።

በምስራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባሕርና የኤደን ባሕር ሰላጤ ደኅንነት ያገባናል ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ ተፅዕኖ ያላቸው ሀገራት በርካታ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ የሚርመሰመሱበት ቀጣና መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ላይ ጥቅሞችም ከንግድ መርከቦች ደኅንነት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የወጪና ገቢ ንግድ ሕልውናን የማረጋገጥ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግብጽ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ለማሳነስ የምታደርገው ደፋ ቀናም ከምቀኝነት የሚመነጭ መሰረተ ቢስ፣ የሀገርን ዕድገትና ማንሰራራት ካለመቀበል የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸውን ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ያሰማሩበት ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን በሌላ ነገር በማጣመድ ዓባይን እንዳትጠቀምና ከሁለቱ የውኃ አማራጮች እንድትነጠል ለማድረግ ባላቸው ጽኑ ፍላጎት ምክንያት እንደነበር አብራርተዋል።

ግብጾች ኢትዮጵያን የሚያሸንፉት በድራማቸው ብቻ ነው ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ዓባይንም ሆነ ቀይ ባሕርን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረትም ለረጅም ጊዜ አልተሳካም፤ ቀጣይም አይሳካም ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከሁለቱ ውሃዎች መነጠል አይቻልም፤ የግብጽ የቀይ ባሕርና ኤደን ባሕረ ሰላጤ የምታደርገው አካሄድ ኢትዮጵያን የሚያስቆማት አይደለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም