የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ያፋጥናል - ኢዜአ አማርኛ
የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ያፋጥናል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2019 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የሚተገበረው የዳመርጆግ-ደወሌ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት፣ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነትና የኢኮኖሚ አጋርነት ይበልጥ የሚያጎለብትና የምስራቅ አፍሪካን ድንበር ተሻጋሪ የመሰረተ ልማት ውጥን እውን የሚያደርግ አቅም እንዳለው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።
ፕሮጀክቱ ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጊዜ በመቀነስ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን የሚያፋጥን መሆኑንም ገልጸዋል።
የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ አጋርነት የሚተገበር ሲሆን፤ ከአንድ ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር በላይ የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን የመያዝ እና የማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል።
ፕሮጀክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አሊኮ ዳንጎቴ በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።
በጅቡቲ ዳመርጆግ እና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚዘረጋው የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የነዳጅ አቅርቦት ሂደት በማሳለጥ የሚወጣውን ወጪ የሚቀንስ መሆኑን ምሁራን ገልፀዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን፣ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ወገኔ ማርቆስ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኤሌክትሪክ ኃይልና በሌሎች መሰረተልማት ትብብር ያላት ናት።
እነዚህ የልማት ትብብሮች የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸው የላቀ መሆኑን ጠቁመው፤ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክትም የትራንስፖርት ጫናን በማቃለል ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የያዘችው ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ እምቅ አቅሞችን ወደ ተግባር እየቀየረች ትገኛለች ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በመንግስትና የግል አጋርነት የሚተገበር በመሆኑ ለቀጣናው ሀገራት በትብብር የመስራት ማሳያ የሚሆንና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማዳን የሚያስችል ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ባላት እምቅ ሀብትና ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ወሳኝ ሀገር መሆኗን አንስተው ፤ ፕሮጀክቱ የመደመር መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በልማት በትብብር የመስራት ፍላጎቱ ማሳያ ነውም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በቀጣናው የሚስተዋለውን የመገፋፋትና የሽኩቻ ባህል በመስበር በመተባበርና በጋራ ማደግ ላይ የተመሰረተ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ ሌሎች ሀገራትም አብሮ የመስራትን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡና በትብብር እንዲሰሩ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም በቀጣናውና በአፍሪካ ደረጃ አርአያ መሆን እንደምትችል ማሳያ ነውም ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁር ደረጄ ደጀኔ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በቀጣናዊ የኢነርጂ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እና የትብብር ማዕቀፎችን ለማጠናከር ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚወስደውን ጊዜ በመቀነስ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን የሚያፋጥን መሆኑንም ገልጸዋል።
ምሁራኑ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በቀጣናዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳድግና ለአፍሪካ ሀገራትም ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።