ኢትዮጵያ -በማንሰራራት ወደ ልዕልና እየገሰገሰች ያለች ሀገር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ -በማንሰራራት ወደ ልዕልና እየገሰገሰች ያለች ሀገር
ኢትዮጵያ የሚመጥናትን ታሪካዊ ቦታ ለመያዝ በማንሰራራት ጉዞ ላይ ትገኛለች። በጊዜ ምሕዋር ውስጥ ሲያጋጥሟት የነበሩ ፈተናዎችንና ችግሮችን በብስለት እየተሻገረች፣ ወደ ተመኘችው ከፍታ በመገስገስ ላይ ናት።
ሀገራችን "አይቻልም" የሚለውን የተስፋ መቁረጥ ትርክት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሰብራለች፤ ለምሥራቅ አፍሪካም የብርሃንና የተስፋ ጭላንጭል ፈንጥቃለች። ያለማንም ዕርዳታ፣ በራሷ ልጆች ሀብት፣ ድካም፣ ዕውቀትና ጥረት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ኢንዱስትሪዎቿን በበቂ ታዳሽ ኃይል የምታንቀሳቅስ፣ አልፎም ለጎረቤት ሀገራት የምታጋራ ሆናለች።በውኃ ሀብቷም በፍትሐዊነት የመጠቀም አዲስ ልምድና ምሳሌነትን ፈጥራለች።
በሌላ በኩል የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ በእጅጉ እየተለወጠ ይገኛል።ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶችን ከመጎብኘት ባሻገር፣የሀገሪቱን ከፍታ የሚመጥኑ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለምተዋል። ከጎርጎራ እስከ ወንጪ፣ ከሀላላ ኬላ እስከ ቤኑና፣ከጨበራ ጩርጩራ እስከ ንጋት ሐይቅ ያሉ መስህቦች አዲስ የቱሪዝም ምዕራፍ ከፍተዋል። ነባር ከተሞቿም በኮሪደር ልማትና በማሻሻያ ሥራዎች ዘምነው፣ የጎብኚዎችን ቆይታ የሚያራዝሙ፣ ማራኪና ሳቢ ሆነዋል።
በግብርናው ዘርፍ ለዘመናት ከነበረው "ከእጅ ወደ አፍ" የአመራረት ዘይቤ በመውጣት፣ ወደ ገበያ ተኮርና ትርፍ ምርት መሸጋገር ተጀምሯል።ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ዓመቱን ሙሉ የማምረት ባህል እየዳበረ መጥቷል።በሌማት ትሩፋት እና በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄዎች የተገኙ ልምዶችም የኢትዮጵያን ሥርዓተ ምግብ በማዘመን ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። የንብ ማነብ፣ የዶሮ እርባታ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በመሠረታዊነት ተለውጠው ከአርሶ አደሩ አልፈው የከተማ ግብርና አካል መሆን ችለዋል።
የማዕድን ሀብቶቻችንም በስፋትና በሕጋዊ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። እንደ ወርቅ ያሉ ውድ ሀብቶች ከሕገ-ወጥ ግብይት ወጥተው የኢኮኖሚው መሠረት እየሆኑ ሲሆን፤ እንደ ኦፓል፣ የድንጋይ ከሰል፣ ብረትና መሰል የማዕድን ሀብቶችንም በስፋት የማምረትና የመጠቀም ልምድ እየጎለበተ መጥቷል።
የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ኢትዮጵያ በሚመጥናት ከፍታ ላይ ለመቀመጥ እያንሰራራች መሆኗን ማረጋገጫ ነው።