ቀጥታ፡

የመስቀል በዓል የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ለመረዳት ልዩ አጋጣሚን ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡-የመስቀል በዓል የኢትዮጵያን ረጅም ዘመን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖታዊ  ክንዋኔዎች በጥልቀት ለመረዳት ልዩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።    

በአካል ተገኝተው በበዓሉ ከታደሙት መካከል ከጆርዳን የመጡት ጎብኚ ሚሼል አካሼው፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በተደረገላቸው ሞቅ ያለ እንግዳ ተቀባይነት ባህል መደመማቸውን ገልጸዋል።

በበዓሉ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ድባብ መደነቃቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ይህንን ውብ በዓል ሲያከብሩት መመልከት ደግሞ ትልቅ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ትላልቅ ሃይማኖታዊ በዓላትን በአካል ተገኝተው መመልከታቸውን የገለጹት ጎብኚው፣ የኢትዮጵያ መስቀል በዓል አከባበር ግን ፍጹም ልዩ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።


 

ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባን ዳግም የጎበኙት ጀርመናዊው ጎብኚ አንድሪያስ ሻይብል በበኩላቸው፣ ከተማዋ በመሠረተ ልማት፣ በግንባታ እና በከተማ ገጽታ ረገድ ያስመዘገበችው አስደናቂ ለውጥ እንደማረካቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለቀጣዮቹ ዓመታት የመኖር እና የሀገሪቱን የልማት እንቅስቃሴዎች በጥልቀት የመመልከት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የመስቀል በዓልም የሀገሪቱን ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊት ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።

መሰል ሀገራዊ ሁነቶች የባህል ልውውጥን ለማጠናከር እና በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጎልበት ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ አንስተዋል።


 

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ በመታደማቸው መደሰታቸውን የገለጹት ከኖርዌይ የመጡት ጎብኚ ጆሩንድ ፊየልቢርኬላንድ፣ በበዓሉ ላይ የተመለከቱት ማራኪ ባህላዊ አለባበሶች፣ ህዝባዊ ተሳትፎ እና የደመቀ ድባብ እጅግ እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሙዚየሞችን፣ ታሪካዊ አውደ ርዕዮችን እና አብያተ ክርስቲያናትን ለመጎብኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

በዓሉን በቦታው በቀጥታ መመልከታቸው የሀገሪቱን ባህልና የክርስትና ታሪክ በጥልቀት ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደሰጣቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም