ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር በዓል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡-የመስቀል ደመራ በሃይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክርና የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ድንቅ በዓል ነው ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ፡፡

የ2019 ዓ.ም የመስቀል በዓል በእምነቱ ተከታዮች፣ በውጭ ሀገር ዜጎችና በርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአዲስ አበባ የመስቀል አደባባይ ተገኝቶ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን የተከታተሉ ታዳሚዎች አነጋግሯል።


 

ካነጋገራቸው ታዳሚዎች መካከል ተተኪ አርበኛ ዋና ሳጅን ስዩም ጌታሁን፤  የመስቀል በዓል ህዝቡ ሃይማኖታዊ እሴቱን የሚያሳይበትና በፍቅር የሚያከብረው ታላቅ ትዕይንት መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ የሃይማኖታዊና የባህላዊ እሴቶች መገለጫ በመሆን ሕዝቦችን የሚያስተሳስር፣ የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብትና የሀገርን በጎ ገጽታ ለዓለም የሚያሳይ ታላቅ በዓል መሆኑንም እንዲሁ።

የመስቀል ደመራ በዓል የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክርና የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ድንቅ ትዕይንት መሆኑን አመላክተዋል።

ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ መምህር ጥበቡ ጋሻው በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው ተሰባስበው በጋራ የሚደምቁበት ልዩ በዓል መሆኑን አንስተዋል።


 

የመስቀል በዓል ከሀገር ውስጥ አልፎ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተገኝተው የሚዘግቡት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ፣ ባህልና እሴት ለመላው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በግልጽ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ታላቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።

የመስቀል በዓልን ስናከብር የምህረትና የፍቅር አርአያ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ በመከተል የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ወይዘሮ አክብረት ካሳሁን ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም