ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ታሪካዊ የንግድ ትስስር የባህር በር ባለቤትነትን ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት ያጠናክረዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በቀይ ባህር በኩል ያላት ታሪካዊ የንግድ ትስስር የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት ያጠናክረዋል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ቀጄላ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን በመነጋገርና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለማስመለስ እየሰራች ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት ዕድገትና ደህንነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው እነዚህ የቀጣናው ሀገራት ትስስራቸውን በማጠናከር በጋራ ማደግና መልማት ይችላሉ ነው ያሉት።

የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ አዲስ እንዳልሆነ አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከቀይ ባህር አካባቢ ካሉ ሕዝቦችና ከውጭው ዓለም ጋር የንግድ ትስስር ስትፈጥርበት የቆየ ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያን ጥያቄ ታሪካዊነት እና ህጋዊነት ያረጋግጣል ብለዋል።

የባህር በር ከሀገሪቱ ህልውና ጋር በጥብቅ የተያያዘ ጉዳይ መሆኑንም አማካሪ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የቀጣናው ሀገራት ዕድገታቸውንና የአካባቢያቸውን ደህንነት በጋራ ማጠናከር እና ተጠቃሚነታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሃዊ መሆኑን ገልፀው፣ ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ሕግና በዲፕሎማሲ መንገድ ለመከታተል የሚቻልባቸው መንገዶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ምሁራንም የባህር በር ጉዳይን እንደ ሀገራዊ አጀንዳ በሰፊው እየመከሩበት እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ፣ ከጂኦግራፊያዊ፣ ከሕዝብ ቁጥርና ከደህንነት ምክንያቶች የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል በሕዝብ ብዛት ትልቅ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፣ በፍጥነት እያደገ ከመጣው የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የንግድ ፍላጎት አንጻር የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው ምክንያታዊ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት ለመከታተልና ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት የራሷን ሚና ለመወጣት የባህር በር ጉዳይ ወሳኝ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን በዲፕሎማሲያዊ መንገድና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርታ እያቀረበች እንደምትገኝም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም