የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉም ያለው እሴት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉም ያለው እሴት ነው
ጎንደር፤መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡- የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉም ያለው እሴት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በወቅቱም ሚኒስትሯ እንደገለፁት፤ የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉም ያለው እሴት ነው።
በዓሉ ከእኛ አልፎ በዩኔስኮ የተመዘገበ የሰው ልጅ ሁሉ ቅርስና ሀገራችን የምትኮራበት ድንቅ ስጦታ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት ከሚረጋገጥባቸው ዓብይ ጉዳዮች አንዱ ሳይበረዙ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩት መሰል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶቻችን ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በጎንደርና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመዳረሻ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውሰዋል።
የትናንት ከፍታችን ማሳያና የነገ ተስፋችን ምልክት የሆኑትን እነዚህን ሀብቶቻችንን እንደ ዓይናችን ብሌን በመጠበቅና ለቱሪዝም ምቹ በማድረግ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ማሳደግ ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉም አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በከፈለው መስዋዕትነት፣ መስቀል የበረከት፣ የክብር፣ የሰላምና የነፃነት አርማ ሊሆን መቻሉን ገልጸዋል።
በመሆኑም አሁን ባለንበት ጊዜ የመስቀሉ ምልክት የሰው ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣበትና ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበት ታላቅ ጸጋ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዓሉን ስናከብር ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም አጥብቆ በመጸለይ፣ የተቸገሩትን በማሰብ፣ እንዲሁም አምላክን በትሕትና፣ በመታዘዝ እና በፍቅር በማምለክ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኛው፤ የመስቀል በዓል ከአባቶች የተወረሰ ታላቅ አደራ፣ የመሥዋዕትነት፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ መሆኑን አብራርተዋል።
የዘንድሮው በዓል ከዓለም የቱሪዝም ቀን ጋር መከበሩ ድርብ ደስታን ይዞ መምጣቱን ገልጸው የጎንደር ከተማ የበዓሉ አከባበር የከተማዋን ጥንታዊ ቅርሶች፣ የንጉሣውያን ግንቦችንና ውብ ባህል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን ለማነቃቃት ዕድልን ፈጥሯል ብለዋል።
ለበዓሉ መሳካት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶችና የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመሥራት አስተማማኝ ሰላም መገንባታቸውን ገልጸው፣ የተገኘው ሰላም ለከተማዋ ልማትና ውበት መፋጠን ታላቅ መሠረት መሆኑንም ጠቁመዋል።