ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፅናትና የአንድነት ምዕራፍ ምሥጢር

ኢትዮጵያ በዘመናት በገነባችው ጠንካራና የማይበገር የአንድነት እሴት፣ የሚገጥሟትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በጽናት በማለፍ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የዘለቀች ታላቅ ሀገር ናት። ታሪካችን በመስዋዕትነት ባንፀባሩቁ ድሎች የታጻፈ አኩሪ ገድል ነው። ታላቅነት ገጻችን የጋራ አብሮነት ሰንደቅ ዓላማዎች የተንጠለጠሉበት ገናና ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያ ታላቅነት የሚመዘነው በመልከዓ ምድራዊ ስፋቷ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቦቿ መሪር ፈተናዎችን በጋራ በመመከት ባሳዩትና አሁንም በሚያሳዩት አኩሪ የፅናት ታሪክ ጭምር ነው።

ትናንት የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ሙከራ ቢያደርግም፣ ኢትዮጵያውያን በውስጥ ባጋጠማቸው ፈተና ውስጥም ቢሆኑ በአንድነት በመቆም ወራሪ ኃይሉን ድል በመንሳት የታላቅ ሀገር ታላቅ ሕዝቦች መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል። ግብፅም ብትሆን የዓባይ መነሻ የሆነችውን ታላቅ ሀገር ለመቆጣጠር በማለም፣ ኢትዮጵያን ለመውረር በተደጋጋሚ ጊዜ ሙከራ አድርጋለች። በኢትዮጵያውያን ጠንካራ የህብረት ክንድ በሃይል ተመታ፣ ተሸንፋና ሀፍረትን ተከናንባ መመለሷ ታሪክ የከተበው እውነታ ነው። በዘመናት መካከል ከአባቶቻቸው የተላለፈው የጀግንነት ምስጢርን ጠላቶቻቸውን ድል በመንሳት በአደባባይ ሲገልጹት ኖረዋል።

አትዮጵያዊያን የልማት ጀግኖችም ናቸው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ ዋነኛ ምስክር ነው። በኢትዮጵያውያን ርብርብ እና ቁርጠኝነት ለውጤት የበቃ፤ ኢትዮጵያውያን ያሰቡትን ከዳር ለማድረስ ዓላማ ከሰነቁ ወደ ኋላ የሚመለሳቸው ምንም ነገር እንደሌለ በተግባር የተገለጠ ሕያው ምስክር ነው። 

ኢትዮጵያዊያን ችግርን በጥበብ የመፍታት ባህል ያላቸው፣ በሀሳብ ልዕልና የሚያምኑ ታላቅ ህዝቦች መሆናቸውን በአደባባይ ያስመሰከሩ፤ ዓለምን ያስደመሙ ታላቅ ህዝቦች ናቸው። ለዚህም ነው ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ሀገራዊና አህጉራዊ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በውጤት ማጠናቀቅ የቻሉት። ይህ ነው የኢትዮጵያውያንን ጠንካራ እሴት አጉልቶ የሚያሳይ ታሪካዊ ኹነት።

ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫም አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች፣ ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት ድምጽ በመስጠት፣ ሥልጣን የሚገኘው በኃይል ሳይሆን በድምጽና በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ብቻ መሆኑን ያሳዩ ስልጡንና በሳል ሕዝቦች መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል። 

ነገን ዛሬ ለመገንባት በጠንካራ ተቋማት፣ በዴሞክራሲያዊ እሴቶችና ዘመንን በመዋጀት ስለመሆኑ በተግባር እያሳዩ ነው። ተፈጥሯዊ ሀብቶቻቸውን፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ለአንድነታቸው፣ ለጋራ ብልጽግናቸው ትእምርት አድርገው የሚጠቀሙትም የያዙትን ታላቅ ርዕይ ለማሳካት ነው። የነገን ብልፅግና እውን ለማድረግ የሚዳሰሰውንም ሆነ የማይዳሰሱ ሀብቶቻቸውን የሚያከብሩ፣ ጀግንነታቸውን በሀሳብ ልዕልና ከፍ የሚያደርጉ ሕዝቦች መሆናቸውን የመጡበት መንገዶች ምስክሮች ናቸው።  

ለዚህ ትናንትና ዛሬ እየተከበረ ያለውን የ2019 ዓም የመስቀል ደመራ በዓልን መመልከት ይቻላል። በዓሉ ለዓለም የተሰጠ በረከት ነው። በዓሉ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የታሪክ ውርስና የታላቅነት መገለጫ ማሳያ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመናን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል፣ ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ ባለፈ፣ ለዘመናት የቆየ ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጸና፣ እንዲሁም የሕዝባችንን ታላቅነት በዓለም መድረክ ያስመሰከረ ነው።  

በደመራ በዓል አከባበር ላይ ኢትዮጵያውያን በዕድሜ፣ በጾታ፣ በማኅበራዊ ደረጃ ሳይገድባቸው በአንድነት ይሳተፉበታል። ይህ በዓላትን አብሮ የማክበር ልማድ ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ኃይል አለው። በዓሉ የሕዝብ አብሮነት ምልክትም ጭምር ነው። በዓሉ ከመከበሩ በፊት ሕዝቡ በዓሉ የሚከበርባቸውን አካባቢዎች በጋራ በማጽዳት እና በደመራው ዙሪያ በመሰባሰብ የጋራ እሴቶቹን ያድሳል። በበዓሉ ወቅት ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ይሰባሰባል፤ አብሮነትና ወንድማማችነት ዳግም ይጠነክራል። በዓሉ ለማኅበራዊ ትስስር እና ለእውነተኛ እርቅ ሁነኛ መድረክ በመሆንም ያገለግላል።

በዓሉ የሚከበርበት መስከረም ወር በኢትዮጵያ የክረምቱ መጨረሻ እና የጸደይ (የበጋ) መጀመሪያ፣ እንዲሁም የአዲስ ዓመት ማግሥት ነው። የልምላሜው ውበት፣ የአደይ አበባ መፍካትና የደመራው ብርሃን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ውበት እና የታሪክ ጥልቀት ለዓለም ያበስራሉ። ደመራ ሲቃጠል የሚታየው ብርሃን፣ ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚወጣው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ በጽናት እንደምትቀጥል ተምሳሌት ሆኖ ይታያል። 

ኢትዮጵያውያን ህብረታቸው የሚፈጥረው ታላቅ ነገር ለዓለም የሚተርፍ ነው። እነርሱ የያዙት ተሻጋሪ ሀብት መሆኑን ለዓለም አስመስክረዋል።

እንደ ደመራው በዓንድነት ስንቆም ያለፈውን ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም በጋራ ልናጸናው የሚገባ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት አርማ አብረን ከፍ እናደርጋለን። አንድነታችን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለትውልድ የሚያሻግር ዘላለማዊ የብርሃን ችቦ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ የአንድነት፣ የትጋት፣ የፍቅርና የመተሳሰብ ምስጢር ከጀግንነታቸው ይመነጫል። በጠላቶቹ የተመሰከረለት ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ መሆናችን ዛሬ ላይ ነገን ለመስራት የምንተጋ ታላቅ ርዕይ ያለን ህዝቦች መሆናችን  የፅናትና የአንድነት ምሳሌ ያደርገናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም