ቀጥታ፡

የጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ፅኑ መሰረት

የኢትዮጵያ የፓለቲካ ስርአት አግላይ መሆኑ ቀርቶ አካታችና አሳታፊ እንዲሁም የህዝብ ጠንካራ ተሳትፎና ባለቤትነት የሚታይበት ሆኗል። በዚህ ረገድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጥሩ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።

ጠቅላላ ምርጫው ሀገርን ለማጽናት የህዝቡ ጽኑ አቋም በተግባር የታየበት ስለመሆኑም መግለጽ ይቻላል። የሀገርን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምርጫ ትርጉም ያለው መሆኑን እያንዳንዱ ዜጋ አምኖ ድምጹን በመስጠት ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጠበቃ መሆኑንም በተግባር አሳይቷል።

የምርጫ ሂደቱ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን የዘላቂ ሰላምና የልማት እንዲሁም ሀገር የመገንባት የጋራ ራእይ የተሰነቀበት ሆኗል። የህዝቡ ይሁንታና ያሳየው ተሳትፎ በሀገሪቱ ፖለቲካ የባለቤትነት ስሜቱ እያደገ መምጣቱንም አመላክቷል።

ከዚህ በመነሳትም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የመንግስት ምስረታና የምክር ቤት የመክፈቻ ስነ ስርአት የሚከናወን መሆኑ ይፋ ተደርጓል። በህዝብ የተመረጠው ብልጽግና ፓርቲም አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቆ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ህዝቡ የሰጠውን አደራ እና አመኔታ በመቀበልም በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል ኪዳን በተግባር ለመፈጸም የሚያስችል ጠንካራ መንግስት ለመመስረት ተዘጋጅቷል።

የመንግስት ምስረታው ህዝባዊ አደራን በብቃት ለመወጣት፣ የልማት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትም ይሆናል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የበርካታ ዘመናት የትግል ውጤት እንደመሆኑ የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ይገባል። በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመመስረት ሂደት የዜጎችን ትብብርና ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ይሄው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በመሆኑም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄደው አዲስ የመንግስት ምስረታ በኢትዮጵያ የጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ፅኑ መሰረት የሚቀመጥበት ታሪካዊ እለት ይሆናል። አዲሱ መንግስትም በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችንና ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን ለማድረግ መትጋት ይጠበቅበታል።

ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የጉባ ብስራቶችን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ውጥኖችን ለስኬት በማብቃት አዲስ ታሪክ ለመስራት እንዲሁም የሀገርን እድገትና ልእልና እውን ለማድረግ ብርቱ ጥረት የሚደረግበት ይሆናል።

በመሆኑም ለሀገር ልማት ስኬት የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የህዝቡ ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም