ቀጥታ፡

በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ ባየናቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተደምመናል

ጎንደር ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡- በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ ባየናቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተደምመናል ሲሉ በጎንደር ከተማ በዓሉን ለመታደም የተገኙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።

የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ጠዋት ላይ የተከናወነውን የበዓሉን ደመራ የመለኮስና ሌሎች ሁነቶችን የታደሙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እንደገለፁት፤ በጎንደር ከተማ በተከበረው የመስቀል በዓል እና በሌሎች አከባቢዎች ባየናቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተደምመናል።

ከእስራኤል የመጡት ራሀሚም ዛይቪር እንዳሉት፤ በበዓሉ የታደመው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳየው ፍቅር፣ ደግነትና አክብሮት የተለየ ነው።

በቆይታቸው ወቅት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በመጎብኘትና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና እሴቶች መዝናናት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለትም በጎንደር በመገኘት የመስቀል በዓል ላይ መታደማቸው ደስታ እንደፈጠረባቸው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ አስደናቂ ጸጋዎች ያሏት ሀገር መሆኗን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

የተመለከቱትን አስደናቂና ማራኪ ሁነት በእስራኤል ለሚገኙ ወዳጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በማካፈል በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚያስተዋውቁም ቃል ገብተዋል። 

ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ጥንታዊ ባህልና ሀገር በቀል እሴቶች በማልማትና ጠብቀው በማቆየት ለኢኮኖሚያዊ እድገት መጠቀም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ሌላኛው ጎብኚ ዳቪድ ራሀሚም በበኩሉ፤ የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት፣ ደግነትና የበለፀገ ባህል አስገራሚ መሆኑን ገልጿል። 

በታላቁ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርና በሀገሪቱ የባህል እሴቶች መደመሙን የገለጸው ዳቪድ፤ የተመለከተውን ውብ ባህል በካሜራ በመቅረጽ በእስራኤል ለሚገኙ ወዳጆቹ እንደሚያካፍል ተናግሯል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኙት ቻይናዊው ጁን ዋንግ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በልዩ ባህላዊ አልባሳት፣ መንፈሳዊ ዝማሬዎችና ክንውኖች በመታጀብ ያከበሩት የመስቀል በዓል ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

"ቀደም ሲል እንደ ግብፅና ሞሮኮ ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ጎብኝቻለሁ" ያሉት ዋንግ፤ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የተለየችና ማራኪ ሀገር መሆኗን እንደሚመሰክሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻይና ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሀገራቱን የንግድና የቱሪዝም ግንኙነት የሚያጎለብት በመሆኑ አገልግሎቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም