መስቀል የይቅርታ፣ የሰላምና የተስፋ ምንጭ - ኢዜአ አማርኛ
መስቀል የይቅርታ፣ የሰላምና የተስፋ ምንጭ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡-መስቀል የይቅርታ፣ የሰላምና የተስፋ ምንጭ
👉የመስቀል ደመራ ታሪካዊ ዳራ
ኢትዮጵያ 19 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስመዝግባለች፤ ይሄውም ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ያደርጋታል። የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ተብለው ከተመዘገቡ የቱሪዝም ሀብቶች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። መስቀል የብዝሃ ማንነት መገለጫ፤ የኢትዮጵያውያን ህብራዊነት ማንጸሪያ፣ የአብሮነት ማስተሳሰሪያ ገመድ፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያከብሩት ሃይማኖታዊ ግን የጋራ በዓል ነው።
መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ መሰቀሉን የሚገልጽ፤ የተጣሉትን ያስታረቀበት መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው። የመስቀል በዓል በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ይከበራል፡፡ የደመራው መደመር አስተምህሮ በ326 ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራኮስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት ደመራ አስደምራ በዕጣን ጭስ ተመርታ ጭሱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ማመልከቱን በማሰብ ነው።
👉መስቀል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ
በአዲስ አበባ የሚገኘው መስቀል አደባባይ የመስቀል ደመራ ሥርዓት አንዱ ማሳያ ነው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን፣ የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑ ሰዎች፣ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት ታላቅ የደመራ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። የመስቀል አደባባይ የደመራ በዓል አከባበር እጅግ ማራኪ፣ ቀልብን የሚስብ ሃይማኖታዊ ሥርዓትና አካሄድ ያለው ነው፤ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ያደረገውም በዚሁ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚከበረው የደመራ በዓል ድምቀት ነው። በዓሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እንደየባህላቸው የተለያየ የአከባበር ሥርዓት አለው።
👉የመስቀል ደመራ በዓል በጉራጌ
የመስቀል በዓል ለጉራጌ ማህበረሰብ የዓመቱ ታላቅ የባህል፣ የሃይማኖትና የዘመነ መሻገር ማዕከል ነው። በተለያዩ ክልሎችና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የጉራጌ ማኅበረሰብ ተወላጆች በዓሉን ወደ ትውልድ ቀያቸው በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያከብራሉ። ወላጆች ከተማ ያሉ ልጆቻቸውን የሚያዩበት፣ የተነፋፈቁ የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበት፣ ሕፃናት አዲስ በተገዛላቸው ልብስ የሚያሸበርቁበት የደስታና የፌሽታ በዓል ነው መስቀል በጉራጌ። መስቀል ያላገቡ ወጣቶች በጭፈራ ወቅት እጮኛ የሚመርጡበትም ዕለት ነው።
በመስቀል በዓል ከብቶች ሳር ታጭዶ የሚቀርብላቸው፣ ጥጃዎች የእናታቸውን ወተት በሙሉ መጥባት እንዲችሉ ላሟ የማትታለብበት የነፃነት በዓል ነው።
በጉራጌ ባህል የመስቀል ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ሁለት ወራት ቀደም ብሎ ይጀመራል። የበዓል ዝግጅቱ መክፈቻም “የቸሃ መስቀል” ይባላል። በቸሃ መስቀል አከባበር ትንሽ የቤተሰብ ደመራ ተለኩሶ በትንሹ የቅርጫ ሥጋ ሥርዓት የበዓሉ መቃረብ ይበሰራል። ከቸሃ መስቀል በኋላ ሴቶች ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ቅቤና አይብ ያዘጋጃሉ። ከጓሮ ጥሩ የተባለውን እንሰት መርጠው በመፋቅ የመስቀል ቆጮ ያዘጋጃሉ። ታዳጊዎች ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውልና ለደመራ መደመሪያ የሚሆን ደረቅ እንጨት ያዘጋጃሉ። አባቶች ከልጆቻቸው ጋር በመተባበር ለመስቀል የሚሆነውን የእርድ እንስሳት በመግዛት ዝግጅቱን ያሟሙቃሉ። ሰዓታት ቀናትን፣ ቀናት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን ተክተው የመስቀል ዋዜማ ላይ “እንኳን አደረሳችሁ” ይላሉ።
በጉራጌ ማኅበረሰብ የመስቀል ደመራ በዓል ዋዜማ “ይፍት” ወይም “የሴቶች በዓል” ይባላል። በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የጉራጌ ተወላጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት የሚደርሱበት ልዩ ቀን ነው። በዋዜማው ለበዓሉ የተነጠረው ቅቤ ይቀመሳል፤ የጎመን ክትፎና አይብ በፍቅር ይቋደሳል።
ከበዓሉ ዋዜማ “ይፍት” እስከ በዓሉ መዝጊያ “አዳብና” የሚቆይ፣ በቄጤማና ስጋጃ የተሠራ ለምግብ ማቅረቢያ የሚያገለግል ባህላዊ ትሪ (ይወደረ) ከተቀመጠበት ወርዶ ይዘረጋል። ከቀንድ የተሠሩ የተለያዩ መጠን ያላቸው የጭልፋና የማንኪያ ዓይነቶች (አንቀፎ) አገልግሎት ላይ የሚውሉበት ዕለት ነው - ዋዜማ፤ በዚህ ዕለት የሚያስፈልገው ወጪ በሙሉ በሴቶች ይሸፈናል።
መስቀል አባቶች የተጣሉትን በማስታረቅ ዓመቱ የሰላም እንዲሆን የሚባርኩበት ነው። በአካባቢው ነዋሪዎች አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሥርዓተ ምርቃት ተከናውኖ ዕርድ ይፈጸማል። በጉራጌ ማኅበረሰብ የመስቀል ዕለት በሁሉም ቤት ይታረዳል፤ በዕርድ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አባቶች ዕርዱን በመባረክ መጪው ዘመን የደስታና የስኬት እንዲሆንላቸው ይመርቃሉ። ከዕርድ በኋላ በቤት ውስጥ የተዘጋጀው አረቄ ቀርቦ ቅምሻ ይበላል። ቅምሻ ዕርድ እንደተፈጸመ ትኩስ ሥጋና ቤት ያፈራው ምግብና መጠጥ የሚቀመስበት የመቋደስ ሥርዓት ነው።
የመስቀል በዓል ማግስት ጥዑም ቡላ ለቁርስ ይቀርባል። በአባቶችና በአካባቢው ሕዝብ ጸሎትና ምርቃት በየቀናውና በየሰፈሩ ትላልቅ የጋራ ደመራዎች ይደመራሉ። ወጣቶችና ታዳጊዎች በከበሮ በታገዘ ጭፈራ በዓሉን ያደምቁታል። አባቶች ፈጣሪያቸው ለትውልዱ፣ ለሀገርና ለቀየው በረከቱን እንዲልክ ሰፊ የጸሎትና ምርቃት መርሃ ግብር ያከናውናሉ።
በመስቀል በዓል በሦስተኛው ቀን የሚከበረው “የሻኛ ቀን” ይባላል። የሻኛ ሥነ ሥርዓት የሚጀምረው በቤተሰቡ አባት ወይም ታላቅ ወንድም ቤት ነው። በዚህ ቀን በየቤቱ የታረደው ሻኛ ወደ ወላጆች ቤት ይሄዳል። ወላጅ ከሌለ ወደ ታላቅ ወንድም ቤት ይወሰዳል። የተሰበሰበው ሻኛ እንደየቤቱ ፍላጎት ተቀቅሎ ወይም በጥሬው በኮባ እየተጠቀለለ እየተሰጠ ይበላል።
ከሻኛ ቀን ጀምሮ ያገቡ ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ወላጆቻቸውን መጠየቅ የሚጀምሩበት የ”ደወቸ” የቤተሰብ ጥየቃ ጊዜ ነው። በመስቀል በአስረኛው ቀን የሚከበረው “ማንጆያ” ወይም “አዳብና” ይባላል። የመስቀል በዓል ማጠናቀቂያ ነው። በዚህ መርሃ ግብር ከኮባ በተሠራ ጊዜያዊ ሰሐን (ጥለስ) የመጨረሻው የቋንጣ ቅቅል፣ ክትፎ ከአይብ ጋር በጋራ በመመገብ የበዓሉ ፍፃሜ ይሆናል።
👉መስቀል የእውነት፣ የፅናት፣ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት
የመስቀል በዓል እውነት ተቀብራ እንደማትቀር ያሳያል፤ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ተራራ ሠርቶ ስለነበር የቀበሩት ሰዎች እንደማይወጣ እርግጠኞች ነበሩ። ተስፋ የቆረጡ አማኞችም አልጠፉም። ብርቱዎች፣ እውነት ፈላጊዎች፣ አቧራውን የሚገልጡ፣ ቆሻሻውን የሚያነሡ ሰዎች ሲመጡ ግን መስቀሉ ከተቀበረበት ወጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ መስቀል ደመራ ዓይነት በዓላት ሃይማኖታውያን ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንስ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫዎች፤ በመደመር ውስጥ ያለውን ጥንካሬና ጉልበት የሚያሳዩ ትውልድ ለእኛ ትምህርት ያቆማቸው ምልክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገራችን ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ወጎች፣ ዐቅሞች፣ ጸጋዎች፣ ሀብቶች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች ወዘተ. ተደምረው ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የባለጸገችና የተከበረች ሊያደርጓት እንደሚችሉ ማሰብ እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ደመራው ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉሙ በተጨማሪ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደ ደመራው ከፍ ብለን እናበራለን” ብለዋል።
እውነት እንደ መስቀሉ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ ሐሰት ኮስምኖ ሐቅ ገንኖ አቧራውን አራግፎ ይወጣል፤ የኢትዮጵያ እውነት አቧራውን ጥሶ፣ አፈሩን አፍልሶ፣ ቆሻሻውን ደርምሶ ይገለጣል፤ ለዚህ ደግሞ ትዕግሥት እንደሚጠይቅ የገለጹት ሀሳብ ግዙፍ መልዕክት መስጥሯል።