ኢትዮጵያ- የዓለም የቱሪዝም ዓይን ማረፊያ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ- የዓለም የቱሪዝም ዓይን ማረፊያ
ኢትዮጵያም በመደመር መንግስት እሳቤ በመመራት በዩኔስኮ ለተመዘገቡ የቱሪዝም ሀብቶቿ የምታደርገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ በማጠናከር፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደብቀው የቆዩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለኢኮኖሚዋ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፤ እንዲሁም ያሏትን ብዝሃ-ባህሎች ለተቀረው ዓለም በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅ በማለም አልምታለች፤ እያለማችም ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት መስፋፋት፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ሀብቶች ሳይበላሹና ሳይደፈርሱ ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።ለዚህም የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ የቱሪዝም አጠቃቀምን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማነት የበኩሏን እየተወጣች እንደምትገኝ የሚያመላክቱ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች።
ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የባህል ልውውጥን የሚያፋጥንና የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ታላቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ነው። ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ሀብቶች ከዘመናዊ አሰራርና ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር አጣጥማ ለዓለም ካቀረበች እና በተገቢው መንገድ ካስተዋወቀች ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማጎልበት በዘርፉ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ ነው።
በዘርፉ እስካሁን የተከናወኑት አመርቂ ተግባራት እና የተመዘገቡ ውጤቶች ለመጪው ዘመን እርሾ በመሆን የሚያገለግሉ ተስፋዎች ናቸው።