የኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ ውብና አስደናቂ ትዕይንት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ ውብና አስደናቂ ትዕይንት ነው
አርባ ምንጭ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ ውብና አስደናቂ ትዕይንት ነው ሲሉ የተለያዩ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ገለጹ።
በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል በትናንትናው እለት በርካታ ምእመናን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በታድሙበት ተከብሯል።
በዓሉ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ጥንታዊ የሃይማኖት፣ የታሪክና የባህል ሃብቶች ለዓለም ህዝብ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ድንቅ አጋጣሚ ነው።
በአርባ ምንጭ ከተማ በነበረው ክብረ በዓል ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ ሀገራት ጎብኝዎችም፤ ክብረ በዓሉ አስደናቂና እጅግ ማራኪ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ የመላው ዓለም ቅርስ መሆኑን እና በተመለከቱት ሁሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ከፖላንድ የመጡት ቶም ማጅ እና ካሮሊና ዱሌክ፤ የኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ በዓል ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ አስደናቂ ትዕይንት ነው ብለዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተመለከቱት አልባሳት፣ ዝማሬውና አጠቃላይ እንቅስቃሴው በተመስጦ የተመለከቱት ትእይንት መሆኑን ገልጸው ማንም ሰው በህይወት ዘመኑ ሊመለከተው የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፖላንድ ዓለም አቀፍ ቱር የቡድን አባላት መካከል ሮበርት ራይቸክ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ታይተው የማይጠገቡ ትውፊቶች፣ አልባሳት፣ ዝማሬዎችና ሌሎችንም የመጎብኘት እድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የመስቀል ደመራ በዓልን ጨምሮ ሌሎች ትውፊቶችንም የመጎብኘት እድል በማግኘቴ በህይወት ዘመኔ የተደሰትኩበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚመጡ ጎብኚዎች እነዚህን ድንቅ ክብረ በዓላት በአካል ተገኝተው እንዲጎበኙና የማይረሳ ልምድ እንዲቀስሙም ጥሪ አስተላልፈዋል።