የቱሪዝም ፀጋዎች ባለቤት ምድረ ገነቷ - አርባምንጭ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ፀጋዎች ባለቤት ምድረ ገነቷ - አርባምንጭ
አርባምንጭ ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡-የቱሪዝም ፀጋዎች ባለቤት ምድረ ገነቷ - አርባምንጭ
አርባምንጭ ከተማ በውስጧና በዙሪያዋ በሚገኙ ድንቅና ውብ የቱሪዝም ፀጋዎች መነሻነት በሀገር ውስጥና በባህር ማዶ ቱሪስቶች "ምድረ ገነት" በሚል ቅጽል ስም ትታወቃለች።
በመሆኑም በውብ የተፈጥሮ ፀዳል፣ በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ሀይቆች የተከበበች፣ ለስሟ መጠሪያ የሆኑ የኤደን አምሳያ ምንጮች የሚፈልቁባት፣ በዕድሜ ጠገብ ጥብቅ ደን የተዋበች የእግዜር ድልድይ መገኛ ፣ የብዝሃ ህይወትና የብርቅዬ ዱር እንስሳት መናኸሪያ፣ የሰላም ተምሳሌት የአኩሪ ህዝብ ባህል ባለቤት ናት አርባምንጭ።
የቱሪስትን ቀልብ የሚያማልሉ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው የስሟ መጠሪያ የሆኑ 40ዎቹ ምንጮች፣ የአባያና ጫሞ ሀይቆች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ዕፅዋፋትና አዕዋፋት ዝሪያዎችን በያዘው የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ፣ የዐዞ ገበያና የዐዞ እርባታ ስፍራዎች እንዲሁም ባህላዊ የዶርዜ መንደሮች ከአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ጋር ተዳምሮ በየማዕዘኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን እያነቃነቁ ይገኛሉ።
👉ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ
ከአርባምንጭ ከተማ በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ 514 ካሬ ኪሎ ሜትር ጠቅላላ ስፋት ያለው ሲሆን ከዚህም 78 ካሬ ሜትር አካሉ በውሃ የተሸፈነ ነው።
በ1967 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ ብሔራዊ ፓርክ ከ91 በላይ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው አጥቢ እንስሳና ከ351 በላይ የተለያዩ የአዕዋፍ ዝሪያዎች እንዲሁም ከ1ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝሪያዎች በውስጡ ይዟል።
በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት መካከል የሜዳ አህያ ፣ ድኩላ ፣ አንበሳ ፣ አጋዘን ፣ አቦሸማኔ ፣ ከርከሮ እና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የስዋይንስ ቆርኬ እንዲሁም ናይት ጃርትና ኋይት ፍልድ ቡሽ የተባሉ የአዕዋፍ ዝሪያዎች የሚገኙ ሲሆን ፓርኩ በአሁኑ ሰዓት ከጉብኝት ስፍራነት ባለፈ የምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
👉የአባያ ሃይቅ
ከአርባምንጭ ከተማ በስተምስራቅ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ1 ሺህ 160 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የሚገኘው የአባያ ሃይቅ 13 ሜትር ጥልቀት አለው።
የአባያ ሃይቅ በውስጡ አግራሞትን የሚጭሩ 11 ደሴቶችን የያዘ ሲሆን ዐዞ፣ ጉማሬ እና የተለያዩ የዓሣ ዝሪያዎችን በውስጡ የያዘው ይህ ሃይቅ ለአርባምንጭ ከተማ ውበትና የቱሪስት መዳረሻነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
👉 የጫሞ ሃይቅ
የጫሞ ሃይቅ ከአርባምንጭ ከተማ በስተደቡብ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሌላኛው የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ሃይቅ ነው።
550 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የጫሞ ሃይቅ ከ10 እስከ 13 ሜትር ጥልቀት አለው።
የ5 ገባር ወንዞች ባለቤትና በማራኪ ተፈጥሮ የታደለው የጫሞ ሃይቅ በውስጡ ካቀፋቸው ብዝሃ ህይወት መካከል ዐዞ ፣ ጉማሬና የተለያዩ የዓሣ ዝሪያዎች የሚገኝበት ሲሆን የጀልባ ሽርሽርና ጉብኝት የሚካሄድበት ተመራጭ መስህብ ነው።
👉 የእግዜር ድልድይ
ከአርባምንጭ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና በተለምዶ "የእግዜር ድልድይ" ተብሎ የሚጠራው ይህ ስፍራ በአባያና ጫሞ ሃይቆች መካከል በመገኘት ሃይቆቹን ያስተሳሰረ እግዜር ሰራሽ ድልድይ ነው።
በዚህ ጉብታ ስፍራ ላይ ሆኖ የሁለቱን ሃይቆች ሁለንተናዊ ይዘት ከመመልከትም በላይ መንፈስን የሚያድሱና እርካታን የሚያጎናጽፉ በርካታ እንስሳትና ዕፅዋት ይገኙበታል።
👉 40ዎቹ ምንጮች
ለከተማው ስያሜ ምክንያት የሆኑ አርባዎቹ ምንጮች ከከተማው በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን ምንጮቹ ከአለታማ ተራራ ስር እየፈለቁ አከባቢው የኤደን አምሳያ እንዲሆን አድርገውታል።
በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነ በመሆኑ ቀዝቃዛና ነፋሻማ አየር በውስጡ አቅፎ ለጎብኚዎች እርካታን ለከተማው ነዋሪዎች ደግሞ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ይለግሳል።
👉የዐዞ ገበያ
በጫሞ ሃይቅ ዳርቻ ላይ የሚገኝ መስህብ ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በርካታ ቁጥር ያላቸው ዐዞዎች በአንድነት በአሸዋማው የሃይቁ ዳርቻ ላይ ፀሐይ የሚሞቁበት በመሆኑ ነው።
👉 የዐዞ ራንች(የእርባታ ማዕከል)
በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው በአሁኑ ሰዓት በጋሞ ልማት ማህበር የሚተዳደረው የአርባምንጭ ዐዞ ራንች(የእርባታ ማዕከል) በ1976 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።
በራንቹ በተለያየ ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ዐዞዎችን ለጎብኚዎች ከማቅረብ በተጨማሪ ለሀገራት የዐዞ ቆዳን በመሸጥ ገቢ እያገኘ ይገኛል።
ዐዞ ከቱሪስት መስህብነት ባለፈ ቆዳው ለጫማ፣ ለቀበቶ፣ለቦርሳ፣ ለዋሌት፣ ለሌዜር ጃኬት እና ለመሳሰሉ ቁሳቁሶች ያገለግላል።
የእርባታ ማዕከሉ ለጎብኚዎች ዐዞን ከማቅረብ በተጨማሪ ጥንቸል ፣ አሣማ ፣ ዘንዶ እና ኤሊንም እያረባ ይገኛል።
👉 የዶርዜ መንደር
የቱሪስትን ቀልብ ከሚገዙ መስህቦች መካከል ሌላኛው ደግሞ የዶርዜ መንደር ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በጨንቻ የሚገኝ ስፍራ ነው።
የጋሞን ማህበረሰብ የሸማ ጥበብ ፣ የባህላዊ ቤት አሠራር ፣ ባህላዊ ጭፈራ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ድንቅ ስፍራ ነው።
👉 የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነው ይህ ሪዞርት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ጉባኤዎችንና ኤግዚቢሽኖችን የሚያስተናግድ ነው።
በተለይም በአባያ ሃይቅ ላይ 360 ድግሪ እየተሽከረከረ የሚንሳፈፈው የጉጌ ሬስቶራንት የዘመኑን ኪነ-ህንፃ ጥበብ በግላጭ ያሳየ ነው።