የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17/2019(ኢዜአ):- ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓልን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ለክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል ይሁንላችሁ ሲል ምኞቱን ገልጿል።
ይህ የመስቀል በዓል ሰላምና ብልጽግናን ይዞ እንዲመጣ የተመኘው ደግሞ በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ነው።
በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃኑ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ ሲል ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የፖላንድ ኤምባሲ የመስቀል በዓል የደስታ እና የሀሴት እንዲሆን መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን የአንድነት መጠናከርን፣ መታደስንና ብሩህ ዘመንን ይዞ እንዲመጣ በኢትዮጵያ የሜሌዥያ ኤምባሲ መልካም ምኞቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ የብሩንዲ ኤምባሲ በበኩሉ የመስቀል በዓል ለእምነቱ ተከታዮች ሰላም፣ አንድነት እና ብልፅግናን ይዞ እንዲመጣ ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ የአርሜኒያ ኤምባሲ በዓሉ የደስታ እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ጀርመን፣ ፓኪስታን፣ አውስትራሊያና አየርላንድ የመስቀል በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፉ ኤምባሲዎች መካከል ይገኙበታል።
በተያያዘም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የመስቀል በዓል የደስታ እንዲሆን ተመኝቷል።
በዓሉ እ.አ.አ በ2013 በዩኔስኮ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን በመረጃው አውስቷል።