ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚጠበቁበት የበርሊን ማራቶን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚጠበቁበት የበርሊን ማራቶን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 17 /2019 (ኢዜአ)፡- 52ኛው የበርሊን ማራቶን ዛሬ ረፋድ ላይ ይካሄዳል።
በሁለቱም ጾታዎች የሚደረጉ ውድድሮች የዓለም የአትሌቲክስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
በሴቶች ትዕግስት አሰፋ፣ ደራ ዲዳ፣ በዳቱ ሂርዻ፣ ዘይነባ ይመር፣ ቦሰና ሙላቴ፣ ምስጋና አለማየሁ፣ በቀለች ጉደታ፣ ጋዲሴ ሙሉ፣ ኤቢሴ አዱኛ፣ አሚናት አህመድ እና አለምአዲስ እያዩ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
አትሌት ትዕግስት አሰፋ እ.አ.አ በ2022 እና 2023 የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ሆናለች።
በ2023 በነበረው ውድድር ላይ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ በመግባት የኬንያዋ ብሪጅድ ኮስጌይ በ2 ሰዓት 14 ደቂቃ 04 ሴኮንድ ይዛው የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ2 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በማሻሻል አዲስ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።
ይሁንና ይሄ ክብረወሰን በአሁኑ ሰዓት በአበረታች ቅመሞች ምክንያት በታገደችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕጌቲች እ.አ.አ በ2024 በቺካጎ ማራቶን ላይ ተስብሯል። 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ በወቅቱ የገባችበት ሰዓት ነበር።
አትሌት ትዕግስት አሰፋ ለሶስተኛ ጊዜ ውድድሩን የማሸነፍ ግምት አግኝታለች።
በባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ሁለተኛ የወጣችው ደራ ዲዳ ሌላኛዋ የምትጠበቅ አትሌት ነው።
የሴቶች የወቅቱ የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊቷ አትሌት ሮዝመሪ ዋንጂሩ ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
በወንዶች ጌታነህ ሞላ፣ ሹራ ቂጣታ፣ ሚልኬሳ መንገሻ፣ ጉዬ አዶላ፣ ሰለሞን ባረጋና ጭምዴሳ ደበሌ ይሳተፋሉ።
በ51ኛው የበርሊን ማራቶን ጭምዴሳ ደበሌ ሶስተኛ እና ጉዬ አዶላ አራተኛ መውጣታቸው የሚታወስ ነው።
የረጅም ርቀት ሩጫ ንጉሱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ መጀመሪያ ላይ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ሳምንት በወጡ መረጃዎች መሰረት በዛሬው ውድድር ላይ አይሳተፍም።
በ51ኛው የበርሊን ማራቶን ያሸነፈው ኬንያዊ አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ በውድድሩ ላይ ይሳተፋል ተብሎ ቢጠበቅም በልምምድ ወቅት በደረሰበት የእግር አጥንት ስንጥቅ ጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ለመሆን ተገዷል።
ኤሪክ ሳንግ እና ሪቻርድ ያቶር ከኬንያ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው።
በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።
በውድድሩ ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች ከ230 ሺህ ዩሮ በላይ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
በተጨማሪም የቦታውን ክብረ ወሰን የሚያሻሽል አትሌት 30 ሺህ ዩሮ፣ የዓለም ክብረወሰን የሚሰብር አትሌት ደግሞ የ50 ሺህ ዩሮ ተጨማሪ ሽልማት ያገኛል።
እ.አ.አ በ1974 የተጀመረው የበርሊን ማራቶን ከዓለማችን ስድስቱ ታላላቅ ማራቶኖች ተርታ የሚሰለፍ ታዋቂ ውድድር ነው።