አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዛሬን ጊዜያዊ ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ መጪው ትውልድ የተሻለች፣ ለኑሮ ምቹ እና በምግብ እራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንዲረከብ የተነደፈ ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ ራዕይ ነው።
በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የሚከናወነው ይህ ዘመቻ፣ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተደምስሶ የነበረውን የደን ሽፋን በመመለስ፣ የአፈር መሸርሸርን በመግታት እና የስነ-ምህዳር ሚዛንን በማስተካከል ረገድ መሠረታዊ ቅያሬ እያመጣ ይገኛል። ዛሬ የሚተከለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋ ኢትዮጵያ ንጹህ አየር፣ አስተማማኝ የውኃ ሀብት እና ለም መሬት እንዲኖራት የሚያስችል መሠረት በመሆኑ፣ የወደፊቱን ትውልድ ከድርቅ፣ ከበረሃማነት እና ከአየር ንብረት መዛባት ስጋት የሚታደግ ብሔራዊ ዋስትና ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ከግብርና ምርታማነት፣ ከኢኮኖሚ እድገት እና ከአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ጋር በመቀናጀት የሚተገበር በመሆኑ፣ ለወደፊቱ ትውልድ የተረጋገጠ የልማትና የህይወት መሰረት የሚጥል ነው።
አረንጓዴ አሻራን የመትከልና የመንከባከብ ባህል በህፃናትና በወጣቶች ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ፣ ሀገርን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲሸጋገር ያደርጋል። በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ ጥረት የዛሬው ትውልድ ለነገው ትውልድ የሚያስረክበው ታላቅ ተግባር ነው።