ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የሀገር ሁነኛ የሀብት ምንጭ እየሆኑ ነው- የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የሀገር ሁነኛ የሀብት ምንጭ እየሆኑ ነው- የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
ጎንደር ፤ መስከረም 16/ 2019 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሕዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት በርካታ ቱሪስቶችን እየሳቡ የሀገር ሁነኛ የሃብት ምንጭ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የቱሪዝም ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጎንደር ከተማ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል ።
ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የሕዝብ በዓላት በርካታ የውጭ ጎብኚዎችን እየሳቡ ይገኛሉ ብለዋል።
የበዓላት አከባበር እሴቱና ውበቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከክልሎች ጋር በመነጋገር ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን አሠራርን የመተግበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን አሠራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የመረጃ መሠረታዊ ግብዓት በመሆኑ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በተደራጀ መልኩ የማሰባሰብ ሥራ ከክልሎች ጋር እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ800 በላይ አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን መለየት የተቻለ ሲሆን፣ ከክልል የቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በመስመር በማስገባትና በማጠናከር የዘርፉን ዕድገት የሚያፋጥኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ መስቀልን የመሰሉ ታላላቅ በዓላትንና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማካሄድ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።