ምእመኑ ከመስቀል ደመራ በዓል መተሳሰብንና አብሮነትን ሊማር ይገባል - ብፁዕ አቡነ ሰላማ - ኢዜአ አማርኛ
ምእመኑ ከመስቀል ደመራ በዓል መተሳሰብንና አብሮነትን ሊማር ይገባል - ብፁዕ አቡነ ሰላማ
ገንዳ ውኃና ደብረ ማርቆስ፤ መስከረም16/2019 (ኢዜአ) ፦ምእመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ምልክት ከሆነው የመስቀል የደመራ በዓል መተሳሰብንና አብሮነትን ሊማር ይገባል ሲሉ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሰላማ ገለጹ።
የመስቀል ደመራ በዓል በገንዳ ውሃና ደብረማርቆስ ከተሞች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሯል።
ብፅዕ አቡነ ሰላማ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የመዳን፣ የፍቅርና የሰላም ምልክት ነው።
በመሆኑም ከመስቀል የደመራ በዓል መተሳሰብንና አብሮነትን መማር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ ፍቅርንና አንድነትን በማጠናከርና ጥላቻን በማስወገድ ሊሆን ሊሆን ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በበአሉ ይቅርታና ፍቅርን በማስቀደም ለአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል።
ከምዕመናን መካከል አቶ ብርቁ ሰማ እንዳሉት፣ የበዓሉን አስተምህሮ በመጠበቅ ለሰላምና አንድነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት አሸናፊ አለሙ በበኩሉ፣ ከበዓሉ ያገኘውን የመቻቻልና የፍቅር እሴት በመያዝ ለአካባቢው ሰላምና እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
በተመሳሳይ የምስራቅ ጎጃም ዞን የአዊና መተከል አሃጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹእ አቡነ ቶማስ ባስተላለፉት መልእክት የመስቀል በዓል የአምላካችን ቸርነቱና ጥልቅ ፍቅሩ የሚታወስበት ነው ብለዋል።
ከመስቀል ደመራ እሴት በመማር ፍቅርና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በበኩላቸው የመስቀል በአል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የቱሪዝም ጸጋ ነው ብለዋል።
የመስቀል በዓል የመደመር ምልክት በመሆኑ በጋራ በመተባበር ለአካባቢያችንና ለሀገራችን ሰላምና ልማት በትኩረት ልንሰራ ይገባል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማን ሰላም፣ እድገትና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የእምነቱ ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል።